Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ እያደረግሁት ያለውን ድጋፍ እቀጥላለሁ – ዩኒሳ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2013(ኤፍ ቢሰ) የደቡብ አፍሪካው ዩንቨርሲቲ ዩኒሳ በኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሬ እቀጥላለሁ ሲል ገለፀ፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ዩኒሳ ተወክለው የመጡ የልኡካን ቡድንን ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይታቸው ዩኒሳ በኢትዮጵያ ትምህርት ዘርፍ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ በተጠናከረ መልኩ በሚቀጥልበት ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
የዩኒሳ ምክትል ሃላፊ ፕሮፌሰር ፕሌንግ ላንካቡላ ዩንቨርሲቲው የሚሰጣቸው ፕሮግራሞች የአፍሪካዊያን እድገት በአፍሪካዊያን እንዲረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ሀገራት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ ለማሻሻል እንደሚሰራ ጠቅሰው÷ በተለይ በኢትዮጵያ ያለውን ተሳትፎ ለማሻሻል ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ ማግኘቱን አንስተዋል።
አፍሪካዊያን በእውቀትና በምርምር ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ እድገት ሽግግር እንዲኖራቸው እንደሚሰራም ነው ተናግረዋል።
የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ሞታ በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲው አሁን ከሚሰጣቸው ፕሮግራሞች በተጨማሪ ሎሎች አዳዲስ ስልጠናዎችን እንዲጀምር ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሚሰጣቸው ፕሮግራሞች የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ስርዓት ውስጥ እንዲያልፉ ስምምነት ላይ መደረሱንም ነው የተናገሩት።
ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ዝርዝር ሁኔታዎች ላይ ከልዑካን ቡድኑ ጋር ምክክር መደረጉን የተናገሩት ደግሞ በኤጀንሲው የእውቅና አሰጣጥ ዳይሬክተር አቶ አብይ ዳባይ ናቸው።
በተለይ እንደ ‘ዩኒሳ’ ባሉ ዩንቨርሲቲዎች በኩል የሚሰጡ ድንበር ተሻጋሪ ትምህርቶች የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ዩኒሳ ከ10 ዓመት በፊት የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን በመያዝ በኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት የጀመረ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መሆኑን ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.