Fana: At a Speed of Life!

ሩስያ መርህ ላይ የተመረኮዘ ድጋፍ በመስጠት ሁሌም ከእኛ ጋር ናት- አምባሳደር ዓለማየሁ ተገኑ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 1፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና ሩስያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን በሩስያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዓለማየሁ ተገኑ ገለጹ።
ሀገራቱ ከ125 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ግንኙነታቸው በተለያዩ መንግሥታት ሥር እያደገ በመምጣት አሁን ላይ ፈርጀ ብዙ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አምጥቷል ብለዋል፡፡
በተለይ የኢትዮ-ሩስያ የጋራ በይነ – መንግሥታት ኮሚሽን መቋቋም ትብብሩና ግንኙነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር አስችሏል ብለዋል፡፡
በተለያየ የትግበራ ምዕራፍ ላይ የሚገኙ ከ20 በላይ የሁለትዮሽ ሥምምነት መፈረማቸውን ገልፀው÷ በቅርቡ ኒዩክሌርን ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰውን ሥምምነት እንደሚያካትት ገልጸዋል፡፡
በኢንቨስትመንት ዘርፍም በርካታ የሩስያ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት ያላቸው ፍላጎታቸው እያደገ መጥቷል ያሉት አምባሳደሩ÷ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በንግድ ዘርፍም አጋርነቱ እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
በባህል ዘርፍ ግንኙነቱ እየተጠናከረ መምጣቱን የገለፁት አምባሳደር አለማየሁ÷ ወደ ሩስያ የሚያቀኑት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችም በዚህ ረገድ ትልቅ አበርክቶ እንዳላቸው ለኢዜአ አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ ዘርፎች ላይ ሩስያ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንድትሰጥ በእቅድ መያዙን ተናግረው÷ ጎን ለጎንም እየተጠናከረ የመጣው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አጋርነት ሌላኛው ማሳየ መሆኑን አንስተዋል።
በፖለቲካው ዘርፍ ኢትዮጵያና ሩስያ ያላቸው ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት አምባሳደሩ÷ ሩስያ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የመደገፍ ሥራ እየሰራች መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በተለይም በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሩስያ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም አጋርነቷን ማሳየቷን ገልጸዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር አጋርነቷን ማሳየቷን ነው የገለጹት።
ሩስያ መርህ ላይ የተመረኮዘ ድጋፍ በመስጠት ሁሌም ከእኛ ጋር ናት ያሉት አምባሳደር ዓለማየሁ÷ ይህ አጋርነቷ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አበክረን እንሰራለን ብለዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.