Fana: At a Speed of Life!

የድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ የሽኝት መርሃ ግብር በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአንጋፋው ድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ የሽኝት መርሃ ግብር በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ነው፡፡

በሽኝት መርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የድምጻዊው ቤተሰቦቹ፣ አድናቂዎች እና የሙያ ባልደረቦቹ ተገኝተዋል።

ድምፃዊው ላለፉት 60 ዓመታት በሙዚቃ ውስጥ ባሳለፋቸው ዘመናት ሁሉ ለኢትዮጵያ ሳይሰለች ሲያገለግል መቆየቱ በመርሃ ግብሩ ተጠቅሷል።

በመርሃ ግብሩ የተገኙት ጸሀፊ፣ ተውኔትና ደራሲ አያልነህ ሙላቱ÷ ሀዘኑ የመላ ኢትዮጵያ ሀዘን ነው ብለዋል።

ድምጻዊ አለማየሁ ለኢትዮጵያ ቀስቃሽ እና አስተማሪ የሆኑ ስራዎችን ሰርቷል ፤ ለአብነትም “ስቀሽ አታስቂኝ የደላሽ ይመስል” የሚለው ሙዚቃ በስድሳዎቹ የወጣቶች ትግል ወቅት እንደ መዝሙር ማገልገሉን አስታውሰዋል፡፡

የሙዚቃ ተመራማሪው ሰርጸ ፍሬ ስብሐት በበኩሉ÷ የዓለማየሁ ስራዎች ለምርምር ስራ በር የከፈቱ መሆናቸውን አስረድቷል።

ዓለማየሁ የሙዚቀኞች ማህበር እንዲመሰረትና የጥበብ ሰዎች መብት እንዲከበር መታገሉንም አክሏል።

በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አክሊሉ ዘውዴ ÷የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከተቀረው ዓለም ጋር በማቀራረብ ዓለማየሁ የጎላ አሻራ እንደነበረው አብራርተዋል።

ይኑር አባብዬ፣ እታበባ፣ ማን ይሆን ትልቅ ሰው፣ ወታደር ነኝ፣ ችግርሽ በኔ አልፏል፣ ሀገሬ ኢትዮጵያ መመኪያዬ፣ ጥቁር አንበሳና ሌሎች ስራዎቹ የነፃነት ታጋይነቱን እና የሀገሩን ፍቅር ያንፀባረቀባቸው ስራዎቹ መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡

ወደ ኮንጎ በመጓዝም ሰላም ለማስከበር ዘምተው ለነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች የማበረታቻ የሙዚቃ ስራዎቹን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ዘርፎች ማህበራት ህብረት ፕሬዝዳንት ክቡር ዶክተር ዳዊት ይፍሩ በበኩላቸው÷ ድምፃዊው የነበሩበትን ጫናዎች አሸንፎ የወጣ እና በመስዕዋትነት ያለፈ መሆኑን አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ለኢትዮጵያ ሲያዜም ስለ ኢትዮጵያ ሲናገር ኢትዮጵያንም በትውልዱ ልብ ውስጥ በመቅረፅ ዓለማየሁ እሸቴ ጉልህ ሚና ነበረው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ በማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙአዘ ጥበብ ዳንኤል ክብረት በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሀገር በፈተናዎች ውስጥ ስትሆን የከያኒውን ሚና በተግባር የገለፁ መሆናቸውን አሳይቷል ብለዋል።

ድምፃዊው “ለኢትዮጵያ ዛሬ ነው መስራት ያለብን” በሚል እሳቤ በቅርቡ ለሀገር ህልውና ሲሰራ እንደነበርም በመልዕክታቸው አስታውሰዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው÷ ኢትዮጵያን የሚወዳት ድምፃዊ ዓለማየሁ፣ ለኢትዮጵያ የመጨረሻውን አበርክቶ ለህዝብ ለማድረስ ሳምንት ሲቀረው ማለፉን አንስንተው፣ ሙዚቀኛውን `ኢትዮጵያን ያነገሰ ሰው` ሲሉ ገልፀውታል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ÷ ዓለማየሁ ሀገሩን በቅንነት ያገለገለ፣ ስለ አገልግሎቱም ኢትዮጵያ ሁሌም የምታመሰግነው ሰው እንደሆነ አንስተው፣ሀገሩን ያገለገለ እንደሚወደድና እንደሚመሰገን ዓለማየሁ ማሳያ ነው ብለዋል።

ከስንብት መርሃ ግብሩ በኋላም የድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ የቀብር ስነ ስርዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን የሚፈጸም ይሆናል።

በአፈወርቅ እያዩ

         

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.