በመዲናዋ ለአዲስ ዓመት የቅድመ አደጋ ዝግጁነት ስራ መሰራቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ ለአዲስ ዓመት የቅድመ አደጋ ዝግጁነት ስራ መስራቱን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ የአዲስ ዓመት በዓልን ጨምሮ የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላትን ተከትሎ ሊከሰቱ ከሚችሉ ማናቸውም ድንገተኛ አደጋዎች ማህበረሰቡን መታደግ የሚያስችለውን የቅድመ አደጋ ዝግጁነት ስራ መስራቱን አስታውቋል።
ይህ የተገለፀው የኮሚሽኑ የአደጋ ምላሽ ዘርፍ ከማዕከሉ እና ከቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶቹ ሰራተኞች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ነው።
ኮሚሽኑ በበኩሉ ቅድመ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ቢሆንም አደጋ ሳይከሰት ቀድሞ ለመከላከል የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ጉልህ ሚና አለው ብሏል።
በመድረኩም በ2014 ከመስከረም ወር ጀምሮ ለሚከበሩት ሶስት በዓላት ማለትም÷ በአዲስ ዓመት፣ በመስቀል እና በኢሬቻ በዓላት ለአደጋ ጊዜ የምላሽ አገልግሎት ለመስጠት የሚውሉ በቂ ግብአቶች እና ተሽከርካሪዎች መመደባቸውን ገልጿል።
በዚህም መሰረት በአስር ክፍለ ከተማ 918 የአደጋ ሠራተኞች ፣ 39 ከባድ የአደጋ ተሽከርካሪዎች እና 22 የቅድመ ሆስፒታል አገልግሎት የሚሰጡ አምቡላንሶች ዝግጁ መሆናቸው ተገልጿል።
ሆኖም ግን ጥንቃቄ እየተደረገ ለሚገጥም ማንኛውም አደጋ :-
በነፃ የስልክ መስመር 939
እንዲሁም በቀጥታ የውስጥ መስመሮች :-
0111555300
0111568601
ወይም 0111264848
ላይ በመደወል አገልግሎቱን 24 ሰዓት ማግኘት እንደሚችሉ ኮሚሽኑ አስታውቋል።