Fana: At a Speed of Life!

በወሎ ግንባር የተሰለፉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሰዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ሕዝብ ላይ ወረራ በመፈጸም ንጹሃንን እየገደለ፣ ንብረት እየዘረፈና መሰረተ ልማት እያወደመ ያለዉን የሽብር ቡድን ለማፈራረስና ለመቅበር የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በየአቅጣጫዉ እየተፋለሙት ይገኛሉ፡፡
የመላዉ ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጠላት የሆነዉን የሽብር ቡድን ለማፈራረስ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሰሜን ፈጥኖ ደራሽ ዳይሬክቶሬት ምክትል አዛዥ ኮማንደር ምትኩ ዳባ ገልጸዋል፡፡
በወሎ ግንባር የተሰለፉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ወራሪውን ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሱበት መሆኑን ኮማንደር ምትኩ አስረድተዋል፡፡
አሸባሪዉ የትህነግ ቡድን በደረሰበት አካባቢ ጥፋት ፈጽሟል ያሉት ኮማንደር ምትኩ÷ ቡድኑ በወረባቦ ወረዳ ጎሃ በተባለች አነስተኛ ከተማ ንብረት መዝረፉን እና ማውደሙን ተናግረዋል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ በከተማዋ ንጹሃንን በግፍ መግደሉንም ገልፀዋል፡፡
በጎሃ አካባቢ በተደረገ ዉጊያ የአሸባሪዉ ትህነግ ቡድን አዋጊ ጄኔራልን ጨምሮ በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት መገደላቸዉንም ነው ያረጋገጡት፡፡
በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሰሜን ዳይሬክቶሬት ዲቪዥን አራት ፈጥኖ ደራሽ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ኢንስፔክተር ሀሰን አብዱ በበኩላቸው÷ ወራሪዉ ቡድን ወደ አፋር ክልል እና ደቡብ ወሎ ዞን ሰርጎ ለመግባት ቢሞክርም የወገን ኃይል ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸዉን ቦታዎች በመያዝ ከፍተኛ ኪሳራ እንዲደርስበት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ከአማራ ሚሊሻ እና ከፋኖ ጋር በመቀናጀት አኩሪ ድል እያስመዘገበ መሆኑንም አዛዦቹ አስታውቀዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ሀገርን ከመፍረስ ለመታደግና ወራሪ ቡድኑን አሳዶ ለመደምሰስ እና መስዋእትነት ለመክፈል ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ዝግጁ መሆናቸዉን ኮማንደር ምትኩ ገልጸዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.