Fana: At a Speed of Life!

በመተከልና ካማሺ ዞኖች በሚንቀሳቀሰው የህወሓት ተላላኪ ቡድን ላይ የመጨረሻ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅታችንን አጠናቀናል-የክልሉ መንግስት

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከልና ካማሺ ዞኖች በሚንቀሳቀሰው አሸባሪው  የህወሃት ቡድን ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚወሰደውን እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ዝግጅት ማድረጉን  የክልሉ መንግስት አስታወቀ።

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ ፤

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከልና ካማሺ ዞኖች የሚንቀሳቀሰው የአሸባሪው የህወሃት ተላላኪ የሆነው ጸረ-ሠላም ኃይል ሽፍትነትን አንዱ የኑሮ አካል በማድረጉ በክልሉ በምንም ሁኔታ ሠላም እንዲኖር አለመፈለጉን በተግባር እያሳየ ይገኛል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን ባለፉት ጊዜያት በተለይም በሁለቱ ዞኖች የጁንታው የሕወሃት ቡድን ቀንደኛ ተላላኪ የሆነውን ጸረ-ሠላም ኃይል የፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ከተወደው እርምጃ ባሻገር የተለያዩ አማራጮችን አስቀምጦ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

የጥፋት ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች በፈጠረው የጸጥታ ችግርና ጥቃት በሰው ሕይወት፣ በአካል፣ በንብረት ከደረሰው ጉዳት ባሻገር በርካታ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል፡፡

የክልሉ መንግስት ችግሩን በሠላማዊ መንገድና በውይይት ለመፍታት ከፍተኛ የሆነ የበጀት፣ የጊዜ፣ የሰው ኃይል በመመደብ ለወራት የዘለቀ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡

በመተከልና ካማሺ ዞኖች ከሚንቀሳቀሰው የጥፋት ቡድኑ አባላት መካከል የተወሰኑት የቀረበውን “ሠላማዊ ድርድር” በመቀበላቸው የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱም ተደርጓል፡፡

ነገር ግን መንግስት በሆደ ሰፊነት እና ንጹኃን ዜጎች አብረው እንዳይጎዱ በሚል ሠፊ ጊዜ ወስዶ ባለፋት ወራት ያስቀመጠውን የሠላማዊ ድርድር ዕድል እንደ ፍርሃትና ሽንፈት በመቁጠር የአሻባሪውን የሕወሃት ቡደን ተልዕኮ ለማስፈጸም የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱት የጥፋት ቡድኑ አባላት ሳይቀር ወደጫካ በመግባት አሁንም ድረስ በንጹኃን ዜጎች ላይ ጥቃት ከማድረስ ባሻገር ዜጎች ደክመው ያፈሩትን ሃብትና ንብረት መዝረፍን አጠናክረው ቀጥለውበታል፡፡

የክልሉ መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በሚንቀሳቀሱ የጥፋት ቡድኖች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስዱ ከዚህ ቀደም ለጸጥታ አካላት ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

የአሻባሪውን የሕወሃት ቡደን ተላላኪ ግን በክልሉ ዘላቂ ሠላም እንዳይኖር ለማድረግ አሁንም ድረስ ከሠላም ይልቅ “ሽፍትነትን” የኑሮው አንድ አካል አድርጎ በመቀጠሉ፣ ንጹኃን ዜጎችን ከመግደል፣ ንብረት ከመዝረፍና ህብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዳይኖር ከማድረግ አልተቆጠበም፡፡

የክልሉ መንግስት እና የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከሃገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከየክልሎች የልዩ ኃይል አባላት፣ ከሚሊሺያ አባላትና ከግል ታጣቂዎች ጋር በመሆን በጥፋት ቡድኑ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚወሰደውን እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከወትሮ በተለዬ ሁኔታ ዝግጅት አድርጓል፡፡

በተለይም በመተከልና ካማሺ ዞኖች ጸረ-ሠላም ኃይሉ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ይህንን አውቀው ራሳቸውን ከጥፋት ቡድኑ እንዲነጥሉ የክልሉ መንግስት በጥብቅ ያሳስባል፡፡

በተጨማሪም መንግስት ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ለሚወስደው እርምጃ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የመንግስትና የግል ታጣቂዎች፣ ወጣቶች፣ እንዲሁም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለህግ ማስከበር እርምጃው ቅድሚያ በመስጠት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ የክልሉ መንግስት እና የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት

ጳጉሜ 04/3013 ዓ.ም

አሶሳ፣

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.