Fana: At a Speed of Life!

አንድነታችንን አጠናክረን ጠላትን እያሳፈርን እንደ አድዋ ድል እንቀዳጃለን – የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አደም ፋራህ አዲሱን ዓመት በማስመልከት ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለረጅም ዘመናት ተጋምደውና ተዋደው፣ ተደጋግፈውና ተዋሕደው የኖሩ ናቸው ብለዋል።
በአብሮነታቸውም በባህል፣ በቋንቋ፣ በብሔር፣ በፖለቲካ አመለካከትና በእምነት ያላቸውን የየራሳቸውን ማንነት ጠብቀው መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡
እንደ ሀገርም የጋራ ታሪክና እሴቶችን እንዲሁም የጋራ ስነ ልቦና እና ሕብረ ብሔራዊ ሀገራዊ አንድነት እየገነቡም ለዛሬ ደርሰዋል ነው ያሉት።
ታሪክ እንደሚስረዳው በጀግኖቿ ተጋድሎ ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯን እና ሉአላዊነቷን አስከብራ ነጻ ሀገር ሆና በታሪክ ማማ ላይ ከፍ ብላ የታየች መሆኗን ጠቁመው÷ አድዋ ላይ የተለኮሰው የድል ችቦ በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩት የአፍሪካ አገሮች ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ቀንዲል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሀገራችን ያለችበት አሁናዊ ሁኔታ ከመቶ ዓመት በፊት ከነበረው የአድዋ የነጻነት ትግል ዘመን ጋር ይመሳሰላል ብለዋል አፈ ጉባዔው፡፡
ለአብነት ዛሬም ሀገራችንን በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ውስጥ ለማስገባት የቋመጡ አካላት መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡
ያኔ አንዳንድ ግለሰቦች ለጣሊያን አድረው በባንዳነት ኢትዮጵያ ሀገራቸውን ለመውጋትና ለማዋረድ ጥረዋል፤
ዛሬም አሸባሪዎቹ የሕወሓት ቡድንና ሸኔ በባንዳነት ሀገራችንን ለማዋረድና ሕዝባችንንም አንገት ለማስደፋት ደፋ ቀና እያሉ ነው ብለዋል፡፡
ይህንን ለመቀልበስና በአድዋ ላይ የተመዘገበውን ታሪክ ለመድገም ዛሬም እንደ ትናንቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድነት በመቆም የሀገራቸውንና ሉዓላዊነታቸውን በተባበረ ክንድ በማስከበር ላይ ይገኛሉ፡፡
ሠላምና የሀገር አንድነት በማስጠበቅ ና የጥፋት ተላላኪዎችን በተባባረ የህዝቦች ተሳትፎ ተግባራቸውን በማምከንና እንደ አድዋ አባቶቻችን በአዲሱ ዓመት ድል እንቀዳጃለን ብለዋል።
በመጨረሻም አዲሱ ዓመት ለብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሠላም እንዲሆንላቸው መመኘታቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.