Fana: At a Speed of Life!

ለፀጥታው ስራ ሲባል ርችት መተኮስ አይቻልም – የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም የከተማችንን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ሃይሎችን ለመቆጣጠር እና ለፀጥታው ስራ ሲባል ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ርችት መተኮስ በፍፁም የተከለከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
የ2014 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም እንዲከበር ወቅታዊውን የፀጥታ ሁኔታ ያገናዘበ ዕቅድ በማውጣት እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ወደ ስራ መግባቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በዚህም የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሀገር መከላከያ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከፌደራል እና ከኦሮሚያ ፖሊስ እንዲሁም ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡
በዓሉ በሰላም እንዲከበር የአዲስ አበባ ፖሊስ ለወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከል ተግባሩ ትኩረት በመስጠት በገበያ እና በመዝናኛ ስፍራዎች እንዲሁም ህዝብ በብዛት በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች የተለያየ የጥበቃ ዘዴዎችን በመጠቀም ኃይሉን ማሰማራቱን ነው የገለፀው፡፡
በበዓል ወቅት የግብይት መጠኑ የሚጨምር በመሆኑ ሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውር ሊያጋጥም ስለሚችል ሰዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስቧል፡፡
ከመጠን በላይ አልኮል ጠጥቶና ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ለትራፊክ አደጋ መንስኤ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ስለሆኑ አሽከርካሪዎች ይህን ተገንዝበው እራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ከአደጋ ተከላክለው ሊያሽከረክሩ እንደሚገባም ፖሊስ አስገንዝቧል፡፡
የመዲናዋ ነዋሪዎች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የ2014 የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም እንዲከበር ለፀጥታው ስራ ስኬታማነት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅም ፖሊስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ህብረተሰቡ የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት ጥቆማ ለመስጠት የአዲስ አበባ ፖሊስ በ 011-1- 11-01-11 እና በነፃ የስልክ ጥሪ 991 እንዲሁም በፌደራል ፖሊስ 011-5-52-63-03 እና በ987 ነፃ የስልክ መስመሮች መጠቀም እንደሚቻል መግለጹን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.