Fana: At a Speed of Life!

በአሻባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶችና ህጻናት ድጋፍ እየተጓጓዘ ነው

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራና በአፋር ክልሎች በአሻባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶችና ህጻናት ከ24 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን ሰብዓዊ ድጋፍ እየተጓጓዘ መሆኑ ተገለጸ።

አሻባሪው ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች ባደረሰው የጥፋት ሴራ ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶችና ህጻናት ከመደገፍ አንጻር የተሰሩ ስራዎችን በተመለከተ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው በተለይ በአፋር ክልል መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙና ድጋፍ የሚሹ ህጻናትና ነፍሰጡር ሴቶችን ጨምሮ 76ሺህ 525 ተፈናቃይ ወገኖች መኖራቸው ተገልጿል።

ከእነዚህ መካከል 459 ለተለያዩ ችግሮች በተለይም ከወሊድ በኃላ በደረሰባቸው ጉዳት ተጋላጭ እንደሆኑና 16ሺህ 836 ያህሉ ደግሞ የስነ ልቦና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተነስቷል።

ሚኒስቴሩ ከገቢዎችና ጉምሩክ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ያሰባሰባቸውን የተለያዩ አልባሳት እንዲሁም ከምግብ ነክ ግብዓቶች ስኳር፣ ፓስታ፣ ሩዝ እና ምስር በአፋር ክልል ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች አገልግሎት እንዲውል ድጋፍ አድርጓል።

በአሁኑ ወቅትም ለተፈናቀሉ ወገኖች አገልግሎት የሚውል አጠቃላይ ግምቱ ከ24 ሚሊየን 909 ሺህ ብር በላይ የሚሆኑ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ቁሳቁሶቹ ከድሬደዋ፣ ጅግጅጋ፣ በአዋሽና ከአዋሳ ከሚገኙ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጣቢያዎች ወደ ክልሎቹ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን ተጠቅሷል።

በዚህም 8 ሚሊየን ብር የሚገመት 8ሺህ 500 ኪሎግራም አልባሳት ወደ አማራ ክልል በመጓጓዝ ላይ የሚገኝ ሲሆን÷ ቀሪው ከ16 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት አልባሳትና ምግብ ነክ ቁሳቁስ ለአፋር ክልል መላኩን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.