Fana: At a Speed of Life!

የሰሜን ሸዋና የደቡብ ወሎ ዞን ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊትና ለፀጥታ ኃይላት የገንዘብ፣ የቁስ እና የእርድ እንስሳት ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የሰሜን ሸዋና የደቡብ ወሎ ዞን ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊትና ለፀጥታ ኃይላት የገንዘብ፣ የቁስ እና የእርድ እንስሳት ድጋፍ አደርገዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን የመንዝ ማማ ምድር ወረዳ ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊትና ለሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ለዘመን መለወጫ በዓል መዋያ ከ12 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ሰንጋዎችና በጎችን በድጋፍ አበረከተ።

የሰሜን ሽዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ታዬ የዞኑ ህዝብ ከዚህ ቀደም በርካታ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው፥ ዛሬም የመንዝ ማማ ምድር ወረዳ ህዝብ ለበዓል መዋያ 40 ሰንጋዎችና 2 ሺህ 445 በጎችን ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን እስኪቀበር ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ምክትል አስተዳዳሪው፥ የቡድኑ እድሜ እንዲያጥር ሁሉም በሚችለው አቅም አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይፉ ሰይድ በበኩላቸው፥ ለሰራዊቱና ፀጥታ አባላት የሚደረገው ድጋፍ ብርታትና ወኔ ከመስጠቱም ባለፈ አንድነታችንን በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን፣ በጥሬ ገንዘብ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሁም የ50 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ቁሳቁስ በማሰባሰብ ለሀገር ህልውና እየተዋደቀ ለሚገኘው የፀጥታ ኃይል እገዛ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የህወሓት ወራሪ ኃይል በደቡብ ወሎ ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች በቅንጅት የሚደርስበትን ምት መቋቋም ባለመቻሉ መፍረጠጡንም ምክትል አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

በርክክብ ስነ ስርአቱ ላይ የሰሜን ሸዋና የደቡብ ወሎ ዞን አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.