Fana: At a Speed of Life!

የአፋር ክልል በአማራ ክልል በጅምላ ለተገደሉ ንፁሃን ዜጎች የተሰማውን ሀዘን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ክልላዊ መንግስት በአሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ጭና ቀበሌ በጅምላ ለተገደሉ ንፁሃን ዜጎች የተሰማውን ሀዘን ገልጿል፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈፀም ዋና ተግባሩ አድርጎት ካሁን በፊት በአፋር ክልል ጋሊኮማ እና በተለያዩ አካባቢዎች እንዳደረገው÷ በአማራ ክልልም በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ በርካታ ንፁሀንን መጨፍጨፉን መግለጫው አውግዟል፡፡
ትህነግ በተለያየ ግንባር ሽንፈትን እያስተናገደ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ንፁሃን፣ ህፃናት፣ አረጋዊያን እና ሴቶችን ሰለባ ያደረገ የዘር ማጥፋት በመፈፀም አረመኔያዊነቱን እና ኢ-ሰብአዊነቱን በተደጋጋሚ በተለያዩ ቦታዎች እያሳየ ነው ተብሏል፡፡
ለዚህም በጭና ቀበሌ የተፈፀመው ጭፍጨፋ ማሳያ ነው ብሏል መግለጫው፡፡
በዚህ ጭፍጨፋ ህይወታቸውን በህወሓት ያጡ ንፁሀን ዜጎቻችን ትልቅ ሀዘን ተሰምቶናል፣ ሀዘናቹህ ሀዘናችን ነው ብሏል የክልሉ መንግስት በመግለጫው፡፡
ንፁሀን በምንም አይነት መስፈርት ኢላማ ሊሆኑ እንደማይገባ በመግለፅ÷ ይህን እኩይ ተግባር ለመቃወም እና ለማውገዝ ሰው መሆን ብቻ በቂ በመሆኑ በየትኛውም ጫፍ የሚገኝ የሰው ዘር በሙሉ ድርጊቱን እንዲኮንነው ክልሉ ጠይቋል።
ዘርን መርጦ ጭፍጨፋ ማካሄድ አውሬነት በመሆኑ ÷ ይህን አረመኔ የሽብር ቡድን ለአገር ራስ ምታት ሆኖ እንዳይቀጥል ኢትዮጵያዊያን በአንድነት የጁንታውን አረመኔያዊ እና ኢ-ሰብአዊ አስተሳሰብ ሊቀብሩት ይገባልም ብሏል።
በጭፍጨፋው ህይወታቸውን ላጡ ንፁሀን ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን የገለፀው የአፋር ክልላዊ መንግስት ፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለአማራ ክልል ህዝብና ለመላው ኢትዮጵያውያን መፅናናትን መመኘቱን ከአፋር ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.