Fana: At a Speed of Life!

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ ጉብኝት በአፍሪካዊ ትስስር የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነው

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የጋና እና ሴኔጋል የስራ ጉብኝት ቀጠናዊ ግንኙነትን የሚያጠናክርና በአፍሪካዊ ትስስር የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በሳምንቱ ውስጥ በተከናወኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጋና እና ሴኔጋል ያደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በአፍሪካ ደረጃ ያለውን የእርስ በእርስ ግንኙነት በተሻለ ሁኔታ ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከሀገራቱ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከፍ ባለ ደረጃ ለማስኬድና አፍሪካዊ ተጠቃሚነትን ለማጠናከር ጉብኝቱ የሚያግዝ መሆኑን ሃላፊዋ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር የነበራት ግንኙነት የቆየና ታሪካዊ መሆኑን ገልጸው÷ የአሁኑም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉብኝት አፍሪካዊ ህብረትን በማከልና በፓናፍሪካኒዝም የተቃኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም ጉብኝቱ ቀጠናዊ ግንኙነትን የሚያጠናክርና በአፍሪካዊ ትስስር የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነው ሲሉም አስታውቀዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነትን ከማጠናከር ጎን ለጎን አፍሪካዊ ብልጽግናን ለማሳካት ብሎም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ከፍ ባለ ደረጃ ለማስኬድ ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዚህ ሳምንት በጋና እና ሴኔጋል ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.