Fana: At a Speed of Life!

በአዲሱ ዓመት በጦርነቱ የተጎዳውን ኢኮኖሚ የሚያካክሱ ስራዎች ይከናወናሉ – አቶ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4 ፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በአዲሱ ዓመት የህወሃት ወራሪ ሃይል በከፍተው ጦርነት የተጎዳውን የክልሉ ኢኮኖሚ ማካካስ የሚያስችሉ የልማት ስራዎች ትኩረት ተሰጥቶ ይከናወናሉ ” ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር አስታውቁ።

አቶ አገኘሁ በእንኳን አደረሳችሁ መግለጫቸው እንዳሉት የ2013 ዓመት እንደ ሃገርም ሆነ እንደ ክልል የተሻለ ማህብራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስራዎች የተከናወኑበት ነው ።

በተለይም አይችሉም አያደርጉትም የተባለው ሃገራዊ ምርጫ ኢትዮጰያና ህዝቦቿ አሸናፊ ሆኖው እንዲጠናቀቅ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

“የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን ያለ የሌለ አቅማቸውን ተጠቅመው ለማደናቀፍ ቢሞክሩም በበሰል አካሄድ ማከናወን የተቻለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ትልቅ ስኬት የተመዘገበት ዓመት እንዲሆን አድርጎታል “ ሲሉም አመልክተዋል።

በውስጥ ጉዳያችን ጭምር ጣልቃ በመግባት ኢትዮጰያን ለማንበርከክ የሞከሩ ሃገራት አጀንዳቸው የከሸፈበትና በውጭ ዲፕሎማሲ ታላቅ ስኬት የተገኘበት ዓመት እንደሆነም ጠቁመዋል።

“ይሁን እንጂ የትህነግ ወራሪ ሃይል አማራን ለማዳከምና ኢትዮጰያን ለማፈራረስ በመከላከያ ሰራዊት ላይ እርምጃ በመውሰድ የከፈተው ጦርነት በሁሉም መስክ በተፈለገው ልክ እንዳንጓዝ አድርጓል” ብለዋል።

ወራሪ ሃይሉ አማራን እንደ ህዝብ በማዳከምና በማጥፋት ኢትዮጰያን ለማፍረስ ይዞት የተነሳው ግብ በበሳል አመራርና በህዝቡ ጠንካራ ርብርብ ሳይሳካ መቅረቱን ተናግረዋል

“ይህን እንጂ አሸባሪው ሀይል በወረራቸው አካባቢዎች ንፁሃንን ያለምንም ርህራሄ በጭካኔ ገሏል፣ ሃብታቸውን ዘርፏል፣ ያልቻለውን በአውድም ለአማራ ያለውን ጥላቻ አሳይቷል” ብለዋል።

እንዲሁም የህክምና፣ የመንግስት የአገልግሎት ተቋማትንና የድርጅቶችን ማንኛውንም ንብረት በደረሰበት ሁሉ በመዝረፍ ልክ አልባ በደል መፈፀሙን ተናግረዋል።

በተለይም በአማራ ክልል በማይካድራ፣ ጭና፣ አጋምሳ እንዲሁም በአፋር ክልል ጋሊኮማ የፈፀመው ግፍ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ያስደነገጠና በታሪክ የማይረሳ መሆኑን አመልክተዋል።

አሸባሪው ሀይል በወረራቸው አካበቢዎች ከ551 ሺህ በላይ ህዝብ ለችግር መጋለጡን ርዕሰ ምስተዳደሩ አስታውቀዋል።

“አሸባሪው ሀይል በእብሪት ተነሳስቶ በከፈተው ጦርነት በጀግናው መከላከያ ሰራዊት፣ በአማራና በሌሎች ክልሎች ልዩ ሃይሎች፣ በሚሊሻና በመላው ህዝቡ ርብርብ በገባበት ሁሉ እየተቀበረ ይገኛል” ብለዋል።

“ወራሪ ሀይሉ ዳግመኛ ጦርነት እንዳያስብና ለአማራም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ስጋት እንዳይሆን አድርጎ በመቅበር በአዲሱ ዓመት የተጀመሩ ስራዎች በአጠረ ጊዜ የማጠናቀቅ ስራ ይሰራል” ሲሉም አስታውቀዋል።

በአዲሱ አመት አሸባሪ ሀይሉ በወረረባቸው አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መልሶ ማቋቋምና የወደሙ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ የመገንባት ስራ እንደሚከናወን አመላክተዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላም ከመገንባት ጎን ለጎን በጦርነቱ የተጎዳውን ኢኮኖሚ ማካካስ የሚያስችሉ የልማት ስራዎች ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚከናወንኑ ርእሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

በክልሉ ጦርነቱ በሌለባቸው አካባቢዎች ጠንካራ የግብርና ስራ ማከናወን እየተቻለ መሆኑን ጠቁመው አሁን ላይ ከወራሪው ሃይል በተለቀቁ አካባቢዎች ደግሞ በቀሪ እርጥበትና የመስኖ ልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

ህዝቡ አዲሱን ዓመት ሲያከብር በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ፣ አቅመ ደካሞችንና ኑሮ የከበዳቸውን በመደገፍና በማገዝ እንዲሁም ማዕድ በማጋራት እንዲሆን አሳስበዋል።

ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ለመላው የኢትዮጰያ ህዝብ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ሲሉም የመልካም ምኞት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.