Fana: At a Speed of Life!

ለዘማች የሠራዊት አባላት ቤተሰቦች የአዲስ ዓመት መዋያ ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ለዘማች የሠራዊት አባላት ቤተሰቦች የአዲስ ዓመት መዋያ ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉን ያደረገው በሴት አመራሮች፣ በምሁራንና በነጋዴ ሴቶች የተመሰረተው “የዘመኑ ጣይቱ” የተሰኘ ማህበር መሆኑ ተመላክቷል።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ሃላፊና የማህበሩ መስራች ወይዘሮ ብዙአየሁ ቢያዝን፤ ማህበሩ የህልውና ዘመቻው በድል እንዲጠናቀቅና በመልሶ ማቋቋም የላቀ ሚና ለመጫወት መመስረቱን ገልጸዋል።

ከተመሰረተ አንድ ወር ያልሞላው ማህበር በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማሰባሰቡን ተናግረዋል።

በዚህም ከ4ሺህ 200 በላይ ቦርሳ እና የውሃ መጠጫ ኮዳ ለአማራ ልዩ ሃይል አባላት ልጆች ድጋፍ መደረጉን አውስተዋል።

ትናንት ደግሞ በወረታ የሚገኙ ጉዳት የደረሰባቸው የሠራዊት አባላትን መጎብኘታቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ ብዙአየሁ÷ በ200ሺህ ብር ለዘማች ቤተሰቦች የዓመት በዓል መዋያ ድጋፍ አድርገዋል።

በዚህም ለ40 የዘማች ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው የበግ፣ 25 ኪሎ ግራም የጤፍ ዱቄት፣ የበርበሬና የሽንኩርት ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው ነጋዴ ሴትችን ወክለው የተገኙት ወይዘሮ ጽጌ ግርማ በበኩላቸው÷ ማህበራቸውን በማጠናከርና በማደራጀት የተጀመረውን ድጋፍ እንደሚያስቀጥሉ ገልጸዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ፤ አሸባሪው ህወሓትን ለመደመሰስ የዘማች ቤተሰቦችንና በግንባር የተሰለፈውን ሠራዊት መደገፍ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

“ድጋፉ ሠራዊቱ ከቤተሰብ ትዝታ ወጥቶ ሙሉ ትኩረቱን ለሀገር ክብርና ለዜጎች ደህንነት ብቻ እንዲያደርገ ያስችለዋል” ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ከ7 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ በማሰባሰብ በግንባር ላይ ለሚገኘው ሰራዊት የዓመት በዓል መዋያ የበሬ ሰንጋ፣ የበግና የፍየል ሙክት እንዲሁም ሌሎች ቁሶችን ዛሬ ልኳል ብለዋል ዶክተር ድረስ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.