Fana: At a Speed of Life!

የጉሙዝ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ”ጓንዷ” በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የጉሙዝ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የሆነው የ”ጓንዷ” በዓል “ለዘላቂ ሠላም እና አብሮነታችን በሚል መሪ ቃል በአሶሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግም የብሔረሰቡ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ የብሔረሰቡ ተወላጆች እንዲሁም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ ኃይማኖት አባቶች፣ የተለያዩ የልማት ማህበራት ተወካዮችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ የጉሙዝ ብሔረሰብ መገለጫ የሆኑ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችን እንዲሁም አሁናዊ ሁኔታዎችን የሚያሳዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጓል፡፡

የጉሙዝ ሕዝብ የራሱ የሆኑ በርካታ ቁሳዊና መንፈሳዊ መገለጫዎች እንዳሉት የተገለጸ ሲሆን÷ ከሌሎች ብሔር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ጋርም በአብሮነትና በመቻቻል ለዘመናት የቆዬ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአሸባሪው የህወሓት ተላላኪዎች የብሔረሰቡን ስም ለማጉደገፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ በመሆኑ ይህንን በጋራ ማውገዝ እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡

የትኩረት ለጉሙዝ ልማት ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገለታ ኃይሉ የጓንዷ በዓል የጎህ መቅደድ ተምሳሌት መሆኑን ጠቁመው÷ አሮጌውን ዘመን አሳልፈን ወደአዲሱ ዓመት ስንሸጋገር አብሮነታችንን እያጠለሹ ያሉ ጥላቻ፣ ቂምና በቀል፣ በዘርና ቀለም የመከፋፈል ሳንካዎቻችንን ነቅለን በመጣል ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የክልሉ ምክርቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ወ/ሮ አለምነሽ ይባስ በዓሉ አሮጌውን ዓመት ሸኝተን አዲሱን ዓመት በተስፋ የምንቀበልበት በመሆኑ÷ መላው የጉሙዝ ሕዝብ ለዘመናት አብሯቸው ከኖረው ሌሎች ወንድምና እህት ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በይቅርታና በፍቅር አብሮነቱን የሚያድስበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሪት ምስኪያ አብደላ፣ ሕዝቡ የበርካታ ማንነቶች ባለቤት መሆኑን ጠቁመው፣ ከእነዚህም ውስጥ አቀዳሚ የሆነውን የ”ጓንዷ” በዓል በአግባቡ ተጠንቶ ለተተኪው ትውልድ እንዲሸጋገር የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከልማት ማህበሩ ጋር በመሆን እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

የጉሙዝ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የሆነው የ”ጓንዷ” በዓል ከፓናል ውይይቱ ባሻገር በተለያዩ ባህላዊ ዝግጅቶችም እየተከበረ እንደሚገኝ ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.