Fana: At a Speed of Life!

በህገ ወጥ መንገድ የኮቪድ -19  ህክምና አገልግሎት  የሰጠ ተጠርጣሪ  በቁጥጥር ስር  ዋለ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦሌ ክፍለ ከተማ  በህገ ወጥ መንገድ የህክምና ፍቃድ ሳይኖረው የኮቪድ -19  ህክምና ማዕከል በመክፈት አገልግሎት እየሰጠ የነበረ ተጠርጣሪ  በቁጥጥር ስር  መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።

ተጠርጣሪው ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋለው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ የህክምና ፍቃድ ሳይኖረው ክሊኒክ በመክፈት የኮሮና ቫይረስ ህክምና ለተለያዩ ሰዎች ሲሰጥ ነው፡፡

የአየር መንገድ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ከቦሌ ክፍለ ከተማ  የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ባለሙያዎች ጋር በሰሩት ጥናት ፥ፍቃድ ሳይኖረው ክሊኒክ በመክፈት የኮሮና ቫይረስ ህክምና አገልግሎት ሲሰጥ የነበረውን ግለሰብ  በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ  እየተጣራበት እንደሚገኝ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወንጀል ምርመራ ክፍል ከተገኘው መረጃ  ለመረዳት ተችሏል።

በክፍለከተማው የወረዳ 2 የምግብ እና መድሀኒት  ቁጥጥር  ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጦና ፥ ግለሰቡ ምንም አይነት የህክምና ፍቃድ ሳይኖረው በራሱ ተነሳሽነት በከፈተው የህክምና ማዕከል የውጪ ሃገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች ጭምር ህክምና ፈልገው መምጣታቸውን ገልፀው  ነርስ ነን የሚሉ ግለሰቦችም  በቦታው ላይ የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ የተገኙ መሆኑን ተና ግረዋል፡፡

በወቅቱ በርካታ መድሀኒቶች  በቤቱ ውስጥ የተገኙ ሲሆን   ለምን አይነት ህመም የሚያገለግሉ መድሃኒቶች  እንደሆኑም  በማጣራት ላይ እንደሚገኙ ሀላፊው ገልፀዋል።

ህብረተሰቡ የጤና እክል በሚገጥመው ወቅት ህጋዊ እውቅና ያላቸውን  የህክምና ተቋማት መለየትና ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ  ህገ-ወጥ አገልግሎት የሚሰጡ አካላትን ለህግ አሳልፎ ከመስጠት አኳያ ህብረተሰቡ የሚያደርገው ትብብር መልካም የሚባል እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት  ነው ማለቱን ከመዲናዋ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.