Fana: At a Speed of Life!

የንጋትን ጎህ ለማየት ድቅድቁን ጨለማ ማለፍ ግድ ነው-አቶ ደበሌ ቃበታ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ አዲሱን ዓመት አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
አቶ ደበሌ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው የንጋትን ጎህ ለማየት ድቅድቁን ጨለማ ማለፍ ግድ ነው ብለዋል፡፡
 
ኮሚሽነሩ አዲሱን ዓመት አስመልክተው ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
 
ጀንበር ወደማደሪያዋ ስትገባ ጨለማ በምድር ላይ ይነግሳል፤ የብርሀን ውበትም ይቦዝዛል ፡፡ ድቅድቁም ጨለማ የማይታለፍ እና የማይነጋ እስኪመስል ድረስም ያስጨንቃል፣ ያስፈራልም፡፡ ነግር ግን ጨለማ ምን ብርቱ ቢሆን ብርሃንን ማሸነፍ አይችልም ፡፡ ጨለማው ጥቂት ጊዜ ነው፡፡ ድንግዝግዙም ወቅት አለው ፡፡
 
የንጋትን ጎህ ለማየት ድቅድቁን እና አስፈሪውን ጨለማ ማለፍ የግድ ነው፡፡ በሀገራችን የተከሰቱት ሁለንተናዊ ችግሮች ከሀገራችን እንዲጠፉም መራሩን መስዋዕትነት መክፈል የማይቀር ነው፡፡ አባቶቻችን የሀገራችን አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ እንዲታነጽ በርካታ መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡ በእኛም ዘመን ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ ለመመለስ በተሰለፍንበት ሙያ ሁሉ አስፈላጊውን መስዋዕትነት እየከፈልን እንገኛለን ፡፡
 
ባለፉት ሶስት ዓመታት ለውጡን የሚያንገዳግዱ አንድነታችንን የሚፈታተኑ በርካታ ችግሮች ገጥመውናል፡፡ አንዳንዶቹን ስናያቸው ተስፋ የሚያስቆርጡ ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን ያለመስዋዕትነት ድል የለም ፡፡ ያለፈተናም ስኬት አይገኝምና ሁሉንም በጽናት እንደምናልፋቸው ጥርጥር የለኝም፡፡ አዲሱም ዓመት ይህ ምኞታችን እውን የሚሆንበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
 
አሮጌው ዓመት ተገባዶ አዲሱ ዓመት ሊገባ ጥቂት ሰዓታት ቀርተውታል፡፡ የአዲሱ ዓመት መጀመሪያው ደግሞ የመስከረም ወር ነው፡፡ መስከረም የተስፋ ወር ነው፡፡ ምድር በአደይ አበባ ታሸበርቃለች፡፡ እንቦሳዎችም ይቦርቃሉ፡፡ ወንዞች ከአፍ እስከገደፋቸው ሞልተው ይፈሳሉ፡፡
 
የጠወለገ የሚመስለው የኢትዮጵያ ተስፋም እንደአደይ አበባ መፍካቱ አይቀርም፡፡ በአዲሱ ዓመት ሰላማችን ተመልሶ እንደእንቦሳ የምንቦርቅበት እንደሚሆንም እተማመናለሁ፡፡ እንደወንዞቻችንም ኢትዮጵያዊነት በሁሉም ልብ ሞልቶ የሚፈስበት ዓመትም ይሆናል፡፡
 
መላው ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን !! በአዲሱ ዓመትም ሰላማችን የሚበዛበት ፣ ልማታችንን የምናስቀጥልበት፣ ብልጽግናችን ዕውን የሚሆንበት እንዲሆን ከወዲሁ እመኛለሁ፡፡
 
መልካም በዓል!
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.