Fana: At a Speed of Life!

ፈተናዎች ሁሉ በድል ተጠናቀው ፊታችንን ወደ ልማት የምናዞርበት እሩቅ እይደለም- አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ አዲሱን ዓመት አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ 2013 ዓ.ም 6ኛ ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ፍጹም ሠላማዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቁ ፤ ሁለተኛ ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ያለምንም ችግር መጠናቀቁ በአመቱ ከተመዘገቡ ታላላቅ ድሎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
በአንጻሩ ደግሞ አፍቅሮተ ንዋይ ያሰከረዉ አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያን ለመበተን የሀገር መከታ በሆነው መከላከያ ሠራዊታችን ላይ በከፈተው ጦርነት ተገደን ወደ ውጊያ የገባንበት አስከፊ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት የተቀጠፈበት በርካቶች ደግሞ ከመኖሪያ ቄያቸው የተፈናቀሉበት አመት ነበር።
ኢትዮጵያን ለመበተን የተከፈተብንን ጦርነት በመመከት በአጭር ጊዜ ውስጥ አሸባሪውን ጁንታ በመደምሰስ ወደ ቀድሞ ሠላማችን እንድንመለስ ፤በጀግናው መከላከያ ሠራዊትና በመላው የፀጥታ ሀይሎች ጎን ከመቆም በተጨማሪ በጦርነቱ ምክንያት ከገዛ ቄያቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በመርዳትና በመደገፍ በዓሉን ማሳለፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ርዕሰ መስተዳደሩ።
አዲሱ 2014 አመት አሁን ያጋጠሙን ፈተናዎች ሁሉ በድል ተጠናቀው ፊታችንን ወደ ልማት የምናዞርበት እሩቅ እንዳይደለ ተስፋ አለኝ ያሉት አቶ ደስታ ሌዳሞ፥ መላው የክልላችን እና የሀገራችን ዜጎች የአከባቢያቸውን ሠላም በመጠበቅ እና ሁሉም በተሠማራበት የሥራ ዘርፍ ጠንክሮ በመስራት የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በዓሉን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖቻችንን በማስብ ፤ የኮቪድ-19 አስከፊነቱን በመረዳት ማህበራዊ ርቀታችንን በመጠበቅ መሆን አለበት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ መጪው አመት የሠላም ፣ የደስታ ፣ የስኬት ፣ የመከባበር ፣ የአንድነት ፣ የመቻቻልና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ በሆነው የጨዋነት ፍቅራችንን የሚገልጽበት እንዲሆን ያላቸውን መልካም ምኞት ገልፀዋል።
በቢቂላ ቱፋ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.