Fana: At a Speed of Life!

“ይህ ክፉ ጊዜ ይለፍ እንጂ በዓል ሁሌም ይደርሳል”- ሀብትና ቀለባቸው በሽብር ቡድኑ የተዘረፈባቸው እናት

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) እማሆይ ሲሳይ ዋጋው የደብረ ዘቢጥ ከተማ ነዋሪ ናቸው። የዛሬን አያድረገውና በየዓመቱ የዘመን መለወጫ በዓል ሲመጣ ቤት ያፈራውን በማዘጋጀት በዓሉን በደስታ ያከብሩ ነበር።
 
“የዘመን መለወጫ ለእኔ ልዩ በዓል ነበር” ያሉት እማሆይ ሲሳይ አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ከተማቸውን በወረረበት ወቅት ሀብትና ቀለባቸው በመዝረፉ በዓልን አስፈላጊውን ነገር አዘጋጅቶ በደስታ ማሳለፍ ቀርቶ የዕለት ጉርስ ማጣታቸውን ተናግረዋል።
 
እማሆይ ሲሳይ እንዳሉት የእሳቸው ንብረት ብቻ ሳይሆን የቀበሌው ነዋሪዎች ሁሉ በሽብር ቡድኑ በመዘረፉ ችግሩን የበለጠ የከፋ ያደርገዋል። “ይህ ክፉ ጊዜ ይለፍ እንጅ በዓል ሁሌም ይደርሳል። ብቻ ሀገራችንን ሰላም ያድርጋት” ነው ያሉት።
 
አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ከተማቸውን በወረረበት ወቅት አቅም በሌለው ጉልበታቸው ወደ ጫካ ገብተው ህይወታቸውን ማትረፍ እንደቻሉም ተናግረዋል። “እንኳን በሕይወት ተረፍን እንጂ ሰላም ካለ በዓል በየዓመቱ ይመጣል” ብለዋል።
 
በወገን ኀይል ብርታት ቡድኑ ከቀያቸው ድራሹ ቢጠፋም በቤታቸው ውስጥ ምንም አይነት ቁሳቁስ እንዳልተረፈላቸው ገልጸዋል። በቤታቸው ውስጥ የነበረው የዓመት ቀለባቸው ሁሉ እንደተወሰደባቸው ነው የተናገሩት። እንኳንስ ለበዓሉ ሊደግሱ ቀርቶ ልጆቻቸውን የሚያበሉት እንደሌላቸው እማሆይ ሲሳይ አዝነው ለአሚኮ ተናግረዋል።
 
አቅም ያለው ወገን ሁሉ ለዕለት ጉርሳቸው እንዲደርስላቸውም ጠይቀዋል። ጎረቤቶቻቸውም ሆኑ የሚኖሩበት ቀበሌ እንዲሁም አካባቢያቸው ሁሉ በሽብር ቡድኑ ስለተዘረፈ ማንም ሊደግፋቸው ስለማይችል ለተጎዱት ሁሉ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊደርስላቸው እንደሚገባ ነው እማሆይ ሲሳይ የተማጸኑት።
 
የመገናኛ ብዙሓኑ የጋዜጠኞች ቡድንም ደብረ ዘቢጥ ከተማን ጨምሮ በየአካባቢው በተዘዋወረበት ወቅት በሽብር ቡድኑ ምክንያት ኅብረተሰቡ ያለውን ቀለብና ሀብት እንደተዘረፈ ተመልክቷል። እያንዳንዱ የነዋሪዎች ቤት ውድመትና ዘረፋ እንደተፈጸመበትም በስፍራው በመገኘት አረጋግጧል።
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.