Fana: At a Speed of Life!

አዲሱ ዓመት በተባበረ ክንድ የጠላትን ግብዓተ መሬት ፈጽመን የሠላም አየር የምንተነፍስበት ይሆናል-ኮ/ጀ/ደመላሽ ገ/ሚካኤል

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ለመላው የፀጥታ አካላት ለ2014 ዓ.ም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አዲሱ ዓመት ከውጪና ከውስጥ በአሸባሪው የህወሓት ጁንታ ቡድንና በተላላኪዎቹ የተከፈተብንን ጥቃት እኛ ኢትዮጵዊያን በተባበረ ክንድ እየመከትን ስለሆነ የጠላትን ግብዓተ-መሬቱ ባጠረ ጊዜ በመፈፀም የሀገራችን ህዝብ የሰላም አየር የሚተነፍስበት እና የሀገሩን ልማት የሚያፋጥንበት እንደሚሆን ጽኑ እምነት አለኝም ነው ያሉት ።

ኮሚሽነሩ በ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ህዝቡን ከጎኑ አሰልፎ የዜጎችን ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በርካታ የፀጥታ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውስዋል።

በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ሊደርስ የነበረውን ጥቃት ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ፌዴራል ፖሊስ መመከቱንና እየመከተም እንደሚገኝ ለአብነት ጠቅሰዋል።

6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሆኖ በሠላም እንዲጠናቀቅ ፌዴራል ፖሊስ ከህዝቡና ከሌሎች የፀጥታና የደህንነት ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር እየከፈለ ድርሻውን በብቃትና በገለልተኝነት ተወጥቷል ብለዋል ።

ከጀግናው የሀገር መከላከያ እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌትና ሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በፀረ-ሠላም ኃይሎች እንዳይደናቀፍ ሌት ተቀን በመጠበቅ ለውጤት እንዲበቁ በማድረግ ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች በጀግንነት ታድጓል፣ በመታደግም ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የጁንታውን ርዝራዦች፣ የኦነግ ሸኔ አባላት እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶችን ከመደምሰሱም ባሻገር የተቀሩትን አድኖ ለፍትህ በማቅረብ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ፖሊስ እየሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ጠንካራ ፕሮፌሽናል ፖሊስ ለመገንባት ተቋማዊ ሪፎርሙን ወደ መሬት በማውረድ በርካታ ተሰፋ ሰጪ ስራዎች በአጭር ጊዜ እየተከናወኑ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡

መጪው አዲስ ዓመት ብሩህና ከዚህ በተሻለ አንፀባራቂ ውጤቶችን የምናስመዘግብበትና የኢትዮጵያ ብሎም የተቋማችንን ከፍታ የምናረጋግጥበት እንደሚሆን ታላቅ እምነት አለኝ ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል።

ሕብረተሰቡ የአዲሱን ዓመት በዓልንና በቀጣይ የሚከበሩትን ሌሎች ታላላቅ በዓላትን ያለምንም የጸጥታ ስጋትና ችግር በድምቀት እንዲያከብር መላው የሀገራችን ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታና የደህንነት አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠው:-

ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና የፀጥታ አካላት እንዲሁም በየግንባር እየተዋደቁ ለሚገኙ ለጀግናው የመከላከያና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሠራዊት፣ የክልል ፖሊስ፣ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.