Fana: At a Speed of Life!

በልማት ስራ ላይ የነበረንን ተሳትፎ በአዲሱ ዓመትም አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በልማት ስራ ላይ የነበረንን ተሳትፎ በአዲሱ ዓመትም አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አዲሱን ዓመት በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ፤በ2013 ዓ.ም በርካታ ፈተናዎችን አስተናግደናል፤ ሆኖም በምክክርና በመግባባት ያቀድናቸውን በተባበረ ክንድ ማሳካት ችለናል ብለዋል፡፡

ይፈርሳሉ ስንባል ተደራጅተን፣እርስ በእርስ ይጨራረሳሉ ሲሉን በመደጋገፍ አንድነታችንን አጠናክረን በጠላቶቻችን ላይ ድል እየተቀናጀን ነው ብለዋል አቶ ሽመልስ አብዲሳ፡፡

የህዝባችን ጥቅም ፣የሀገርን ሉአላዊነት እና ነጻነትን ማስከበር ወሳኝ በመሆናቸውም ያለድርድር እየሰራን እንገኛለን ያሉ ሲሆን ÷ዛሬ የአዲሱን ዓመት ዋዜማ ስናከብርም ሳንዘናጋ የሀገራችንን ሰላም መጠበቅ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ትኩረታችን ሁሉ የሀገራችንን እና የህዝባችንን ሰላም ላይ መሆን አለበት ያሉት አቶ ሽመልስ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ለሁሉም የጸጥታ አካላትም እንኳን ለአዲስ ዓመት ዋዜማ በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

እናንተ የታሪክ ጀግኖች ለህዝባችሁ ነጻነት እና ለሀገራችሁ ሉአላዊነት መሰዋትነት በመክፈል እያስመዘገባችሁት ባለው ድል ታሪካችሁን በደማቅ ቀለም እየጻፋችሁ ነው ሲሉም በመልዕክታቸው አስፍረዋል፡፡
እኛም ለእናንተ አደራ ታምነን ባለንበት ሁሉ ከቤተሰቦቻችሁ እና ከዘመዶቻችሁ ጋር ማዕድን ለመጋራት ወስነናል ብለዋል፡፡

ይህ ተግባር በበዓላት ወቅት ብቻ የሚፈፀም ሳይሆን የዕለት ተዕለት ተግባር እንዲሆንም ለክልሉ ህዝብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል አቶ ሽመልስ አብዲሳ በፈተናዎች ውስጥ የሰራናቸው ስራዎች አመርቂ ስለነበሩ በቀጣይም ያለአንዳች መዘናጋት በልማት ስራ ላይ የነበረንን ተሳትፎ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም 11 ሺህ ፕሮጅክቶችን በማጠናቀቅ ለአግልግሎት አብቅተናል ያሉት ርእሰ መስተዳደሩ ለ2014 ዓ.ም ስራችን መሰረት በማድረግ የብልጽግና ጉዟችንን እንደምናሳካ ምንም ጥርጥር የለንም ብለዋል፡፡

በአዲሱ ዓመት የሀገር ውስጥ ምርቶችን በእጥፍ በማሳደግ የዋጋ ንረቱን እና የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም እንደሚሰራና በርካታ የስራ እድልም እንደሚፈጠር የገለፁት አቶ ሽመልስ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ተግባርም ወደ ሌላ ምዕራፍ እናሻግራለን ብለዋል፡፡

በመጨረሻም በ2013 ዓ.ም ህዝቡ በተፈጥሮ እና በስው ሰራሽ አደጋዎች ለአደጋ ለተጋለጡ ወገኖችን ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው መጪው 2014 ዓ.ም የስኬት፣የድል እና የብልጽግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.