Fana: At a Speed of Life!

የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት አባቶች ለ2014 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት አባቶች ለ2014 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ማቲያስ፤ አዲስ ዓመት ሲመጣ የደስታና የተሐድሶ ዘመን እንዲሆንልን ከመመኘቱ ጋር በብሩህ ተስፋ መቀበላችን መልካም ነው ብለዋል።
የሠላምና የእድገት ምኞታችን ወደ ተጨባጭ ፍሬ ሊደርስ የሚችለው በሥራ ብቻ ነው ያሉት ፓትሪያርኩ የተፈጠርነው ለሥራ እንጂ እንድንተኛ ባለመሆኑ በሥራችን ላይ ቸልተኛነት አያሻም ብለዋል።
ዘመኑ አዲስ ሊሆን የሚችለው በምናበረክተው ሥራ እንጂ ዘመን በራሱ አዲስ አይሆንም፤ አዳዲስ ሥራዎችና አሠራሮችን በመፍጠር አዲሱ ዓመት በሁለመናው አዲስ እንዲሆን ተግቶ መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስም ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያዊያን ጥሩ ልማድ የነበራቸውን ሕዝቦች መሆናቸውን አስታውሰው፤ በተጠናቀቀው ዓመት የተስተዋሉ የማይገቡ ተግባራትን ኮንነዋል።
በአዲሱ የ2014 ዓ.ም ያልተገቡ ድርጊቶች ተወግደው በመልካም ተግባራት፣ በመተዛዘንና በአብሮነት መኖር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በጳጉሜን አምስት ቀናት በከፍተኛ አመራሮች የተተገበሩ መልካም ስራዎች ሁልጊዜም መቀጠል አለባቸውም ብለዋል።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የዛሬ እውቀት መስመሩን እየሳተ ሕዝብን ከመጥቀም ይልቅ ለጉዳት እየዳረገ ነው።
እውቀት አለን የሚሉ ሁሉ ለህዝብና ሀገር እድገት ካልሆነ ከማይሃምነት የማይሻል ነው።
በመሆኑም መሪዎች፣ ምሁራኖች ወጣቶችን ሁሉም ለሀገሩ ህዝብ እድገት በጋራ መስራት ይገባዋል ሲሉ መልዕክት አስተላፈዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ በበኩላቸው መጪው ዘመን ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ስለ ሠላምና እርቅ የሚሰሩትን እንደየ እምነታችን የምናበረታታበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
“በአዲሱ ዓመት የጥላቻ ንግግር የሚያባብሱ መረጃዎች ተወግደው ፍቅርና እርቅን የሚሰብኩ ተግባራት ላይ የሚተኮርበት ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
አዲሱ ዓመት ድሆችን፣ የተቸገሩትን፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትንና የተሰደዱትን በመርዳት ክርስቲያናዊ ግዴታን መወጣት እንደሚያስፈልግም አክለዋል።
“ለአገር ሠላምና እድገት መፍትሄው አንድነትን ከሚያናጋ ተግባር መራቅ ነው” ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሐፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ ናቸው።
ከምንም ነገር በላይ ጠላትን ድል ማድረጊያው በትር የሕዝብ በአንድነት መቆም መሆኑን ተገንዝቦ በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ተናግረዋል።
መጪው ዘመን የተጀመሩ ልማቶች ተጠናቀው ጦርነትና መከፋፈል ተወግዶ በአንድነት መሻገር የሚቻልበት እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
አዲሱ ዓመት “የአገር ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ በአንድነትና በመደጋገፍ ተግተን የምንሰራበት፣ ድህነትን ታሪክ የምናደርግበት ይሆን ዘንድ እንቅስቃሴያችን ሁሉ በማስተዋልና በመመካከር ይሁን” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ፤ የተጠናቀቀወ ዓመት ኮቪድን ጨምሮ አገሪቷ በርካታ ተግዳሮቶችን ያስተናገደችበት እንደነበረ አውስተዋል።
በአንጻሩ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትና ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሠላማዊ መንገድ የተካሄዱበት የስኬት ዓመት ነበር ብለዋል።
በመጪ አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ፤ አዲስ ራዕይ ይዘን ሠላምን ተቀዳሚ ተግባር አድርገን መሻገር አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ፓስተር ፃዲቁ።
የጦርነት በጎ ገጽታ የለውምና ሁሉም ዜጋ ለሠላም መስፈን የበኩሉን ድርሻ ሊያበረክት እንደሚገባም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
+4
0
People Reached
0
Engagements
Boost Post
Like

 

Comment
Share
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.