Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ በክረምት በጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ያሳደሳቸውን የአቅመ ደካማ ቤቶች አስረከበ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ካዛንቺስ በክረምት በጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ያሳደሷቸውን የሁለት አቅመ ደካማ ቤቶችን ግንባታዉን በማጠናቀቅና ቁሳቁስ በማሟላት አስረክበዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ÷የክረምት በጎ ፈቃድ  በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተጀምረዉ ወደ ስራ  ከተቀየሩ ትልልቅ ሃሳቦችን አንዱ  መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

“ሀሳቡን ወደ መሬት አዉርደን በዚህ መንገድ ማጓዛችን ከተባበርን ምን መስራት እንደምንችል ትምህርት ያገኘንበትና ሌሎች ትልልቅ ሃገራዊ የሆኑ ጉዳዮችን በትብብር መስራት እንደሚቻል ያሳየንበት  ተግባር ነዉ” ብለዋል፡፡

ለሚኒስቴር መ/ቤቱ 45 የመንግስት ዩኒቨርሺቲዎችም በተመሳሳይ መልኩ የክረምት በጎ ፈቃድ ስራ እያከናወኑ ነዉ ያሉት ሚኒስትሩ÷ በቀጣይም ሌሎችን ተግባራትም አጠናክረን እንቀጥላለን በማለት  ለሰሩ፣ ለመሩና ለተባበሩ ሰዎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸዉ ÷“ከተባባርንና ጥቂት ነገር ካዋጣን የተሻለ ሃገር መፍጠር እንደምንችል ማሳያ ነዉ፤ ካለን ትንሽ ነገር ላይ ቀንሰን ለተወሰኑት መድረስ እንችላለን፤ይህንንም በየአመቱ እየሰራን ከሄድን ዜጎችን የተሻለ ኑሮ ደረጃ እንዲደርሱና የተሻለ ኑሮ መምራት እንዲችሉ ማድረግ እንችላለን” ብለዋል፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን በፍቅር ከተጋገዝን አሁን ያለብንን ችግር አይደለም ሌሎችን መጋፈጥና መሻገር እንደምንችል ያሳየ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል ረዲ በበኩላቸዉ÷ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሰራዉ ስራ የአቅመ ደካሞችን ቤት አፍርሶ ከብርድና ዝናብ መከላከል ከእገዛዉ ሁሉ ትልቅ እገዛ ነዉ ፤ይህም በአዲስ አመት መልካምነትን ያሳየንበት በጋራ የተባበርንበት ነዉ ብለዋል፡፡

የቤት እድሳት የተደረገላቸዉ ወ/ሮ እየሩሳሌም ወንድሙና ወ/ሮ አባይነሽ አለሙ ከዛሬ ነገ ፈረሰብን እያልን እንፈራና እንጨነቅ ነበር ፤ ፈጣሪ ይመስገን ይህን የመሰለ ቤት ስለተሰራልንና ሙሉ የቤት ቁሳቁስና እንዲሁም የበአል መዋያ የበግ ስጦታ ስለተሰጠን  ደስ ብሎናል እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.