Fana: At a Speed of Life!

ራሷን የቻለችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በአንድነት ፀንተን እንቁም -አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ራሷን የቻለችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን በማድረግ በአንድነት ጸንተን እንቁም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን አዲሱ ዓመትን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣

አስቀድሜ፣ ይህንን የ2014 አዲስ አመት የእንኳን አደረሳችሁ ሠላምታና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቴን በራሴና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስም ሳስተላለፍ ከፍ ያለ ክብርና ታላቅ ደስታ ይሰማኛል።

አዲስ አመት በኢትዮጵያውያን መንፈስ የለውጥ መገለጫ እንደመሆኑ ከፀሃይ ብርሀን እና ከምንወዳት ኢትዮጵያ በቀለማት ያሸበረቀ መልክዓ ምድር ጋር ይመጣል።

ይህም አዲስ አመት በአዲስ መንፈስ ከፍ የምትሉበት፣ እንዲሁም በወንድማማችነትና በአንድነት የምትደምቁበት እንዲሆንላችሁ ልባዊ ምኞቴን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፡፡

ባለፈው አመት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ አሰራርና ሙሌት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የአገራችንን ሉአላዊነት ለማጠበቅ ያለንን አንድነትና ቁርጠኝነት በሚያንጸባርቅ መልኩ አከናውነናል፡፡

ግድቡን በምንገነባበት ወቅትም በገንዘብም ይሁን በቴክኒክ ድጋፍ ሁላችንም የበኩላችንን በተሻለ ደረጃ ከማበርከት ወደኃላ አላልንም፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን ባደረጉት ርብርብ እጅግ ተደስታቸለሁ፡፡

በሚቀጥሉት ዓመታትም የበለጠ አስደናቂ ውጤቶችን እንድንመዘግብ ይህንን ታላቅ ሃገራዊ ፕሮጀክት መደገፋችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ አሳስባለሁ፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የህዳሴው ግድብ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የአሸናፊነት ነጥቦችን እንድናስመዘግብ የጎላ ሚና የተጫወቱትን ዲፕሎማቶቻችንና ከተለያዬ ዘርፍ የተውጣጡትን ባለሙያዎቻችንን ልናደንቃቸውና ልናመሰግናቸው ይገባል፡፡

እንዲሁም “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች” የሚለውን እሳቤ ይዘን ባደረግናቸው ተከታታይ ውይይቶችና ድርድሮች በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚመራውን የድርድር ሂደት እውን ለማድረግ እና የህዳሴ ግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር በመርሆዎች ስምምነት መሰረት እንዲሆን የተደረገውን ጥረት እናደንቃለን፡፡

ሁለተኛው የህዳሴ ግድብ ሙሌት ኢኮኖሚዊ እድገታችንን ለማነቃቃትና በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከድህነት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት ያነገብነውን የብልጽግና ተልእኮ ከግብ ለማድረስ አንድ ትልቅ ምዕራፍን የተሻገርንበት ነበር፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ያስመዘገብነውን ስኬት እያየን ዋናውና የመጨረሻ ግባችንን መርሳት አይኖርብንም፡፡

ገና ብዙ ስራ እንደሚጠብቀን አስተውለን በተባበረ ክንድ የብልጽግና ህልማችንን እውን እናደርገዋለን፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን፣

ያለፈው አመት ኢትዮጵያውያን የውስጥና የውጪ ተግዳሮችን በመቋቋም ጽናታቸውንና መንፈሰ-ጠንካራነታቸውን ከፍ አድርገው ያሳዩበት አመት ነበር፡፡

ከዚህም በላይ ህዝባችንን ከዳር እስከ ዳር ያስደነገጠው የጥቅምት 24ቱ የኢትዮጵያ ጠሉ ከሃዲ ቡድን የምሽት ጥቃት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ምልክትን ጥሎ ያለፈ ክስተት መሆኑን ኢትዮጵያውያን መቼም ቢሆን አይረሱትም፡፡

በዚህ ደርዝ ባጣ ድፍረቱና ጨካኝ ድርጊቱ በሰሜን እዝ የነበሩ በርካታ ጀግና ወታደሮቻችንን አጥተናቸዋል፡፡

ይሁንና የሀገራችን ቀንደኛ ጠላት ከሆነው ህወሃት የተቃጡብንን ተግዳሮቶች በሚገባ በመመከትና ከጠላቶቻቸን በተቃርኖ የቆመ የተባበረ ህዝባዊ ግንባርን በመፍጠር ጀግኖቻችን ለከፈሉት መሰዋትነት አክብሮትን አሳይተናቸዋል፡፡

አሁንም ቢሆን በወያኔ የተደቀኑብን ፈተናዎች ገና አላለቁም፡፡ በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች ያሉ ወገኖቻችን ከአሸባሪው ቡድን ቀንበር ነጻ መውጣታቸውንና ተፈናቃዮች ወደ የቀድሞ የመኖሪያ ስፍራቸው እንዲሁም የተጎዱ ሰዎችም ወደ መደበኛ ህይወታቸው መመለሳቸውን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡

ይህን ስናደርግ በእርግጠኝነት ቁስሎቻችን ይፈወሳሉ፡፡

በአማራና በአፋር ክልሎች የሚገኙ አረጋውያንን፣ ሴቶችን እና ሕፃናትን ጨምሮ በንፁሃን ዜጎች ላይ በተፈጸመው ግፍ እና ኢሰብአዊ ግድያ የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽኩ እነዚህን ትርጉም የለሽ ግድያዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ሁሉም ሰላም ወዳድ የሆነ ሁሉ እንዲያወግዝ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

ጠላቶቻችን እኛን ለውጭ ጥቃት ተጋላጭነት ከመዳረጋቸው ባሻገር በኢኮኖሚያችንን ላይም መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ከፍተውብናል፡፡
ሆኖም ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት እንዲያደናቅፉት በፍጹም መፍቀድ የለብንም፡፡

እነርሱ መሠረታዊ የፍጆታና ልዩ ልዩ የመገበያያ እቃዎችን በማከማቸት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬን ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች በማስተላለፍ የልፋታችንን ፍሬ ሊያሳጡን የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ይህንን ደባ ይበቃል የምንልበት ጊዜው አሁን ነው። ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ላሉ ወዳጅ ዘመዶች ገንዘብ በምትልኩበት ጊዜ በሕጋዊ የገንዘብ ማስተላለፊያ ተቋማት በመጠቀም ኢትዮጵያን እንድትደግፉ አሳስባለሁ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ እውነትን ሰንቃችሁ ለአገራችሁ ኢትዮጵያ በታማኝነት እና ሉዓላዊነትዋ እንዲከበር በጽናት ከጎናችን ለቆማችሁ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አባላትና መላው የኢትዮጵያ ወዳጆች ጥልቅ ምስጋናዬን ለመግለጽ እወዳለሁ።

ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፣

በመካከለኛው ምስራቅ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ወገኖች እየደረሰባቸው ያለውን ችግር እንረዳለን። ለዚህም አስፈላጊውን እገዛ ከማድረግ ባለፈ፣ በሺዎች የሚቆጠሩትንም ወደ ሀገራቸው መመለሳችንን አጠናክረን ቀጥለናል፡፡

የኮቪድ ወረርሽ ከስደተኞቹ ብዛት ጋር ተዳምሮ እርዳታ ለሚፈለጉ ዜጎቻችን ሁሉ ለመድረስ አቅማችንን ቢፈታተነውም በቻልነው ሁሉ ልክ እየተንቀሳቀስን ነዉ፡፡ በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ከሀገር ውስጥና ከአለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሮችን ለመቅረፍና ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት እንደሚሰራ ቃል እገባለሁ፡፡
ውድ ኢትዮጵያውያን፣

በርካቶች ተዓማኒና ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል አቅማችንን ተጠራጥረውት የነበር ቢሆንም ለሰላም ጥልቅ ፍቅር ላለው ኢትዮጵያዊ ምስጋና ይግባና፣ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ያለማንም ከልካይነት፣ በነጻነት ድምጻቸውን የሰጡበትና አሻራ ያስቀመጡበት መሆኑን አስመስክሯል፡፡

የምርጫው ውጤትም በአዲሱ አመት ወርሃ መስከረም መጨረሻ ልናቋቁመው ላለው አዲስ መንግስት የኢትዮጵያውያን የማስተማመኛና የማስረገጫ ማህተሞች ናቸው፡፡

ይህንንም እውን ለማድረግ ኢትዮጵያውያን ሰላምን፣ ብልጽግናንና ህብረትን መርጠዋል፡፡

ስለሆነም ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት በማድረግ እና ባለፉት ሶስት አመታት የጀመርናቸውን ዘርፈ ብዙ ተሃድሶዎችን በማፋጠን የብልጽግና ህልማችንን እውን እናደርገዋለን፡፡

በዘህ ወቅት ለሁሉም ኢትዮጵያዉያን የማስተላልፈዉ ዋንኛ መልክት ራሷን የቻለችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ልዩነቶቻችንን ሁሉ ወደ ጎን በማድረግ እጅ ለአጅ እንድንያያዝና በአንድነት ጸንተን እንድንቆም ነዉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገራችን ዋና ተቋማት መካከል አንዱ እንደመሆኑ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው የተሃድሶ ሂደት ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

እየተካሄደ ያለው ሪፎርም ለሀገራችን የበለፀገ የዲፕሎማሲ ታሪክ የሚመጥን ጠንካራና ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሰራተኞችን ይፈጥራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በመተባበር አገራቸውን እንደ አምባሳደር እንዲቆሙ ጥሪ አቀርባለሁ።

ተሃድሶው በሁለትዮሽም ሆነ በባለብዙ ወገን ዘርፎች የምንወዳትን አገራችንን ጥቅሞች ለመጠበቅ እና ለማስተዋወቅ ይረዳናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

በመጨረሻም አዲሱ አመት ለሁላችሁም የሠላም፣ የጤና፣ የደስታና የብልጽግና ይሆንላችሁ ዘንድ ከልብ እመኛለሁ፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.