Fana: At a Speed of Life!

ሰራዊቱ በሚቀዳጀው ድል የወሎ ህዝብ በግንባር ተሰልፎ ያደረገው ተጋድሎ በታሪክ የሚዘከር ነው – አቶ ብናልፍ አንዷለም

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአገር መከላከያ ሰራዊት በአሸባሪው ህወሃት ላይ በሚቀዳጀው ድል የወሎ ህዝብ በግንባር ተሰልፎ ያደረገው ተጋድሎ በታሪክ የሚዘከር ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም ተናገሩ።

የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች የአዲስ ዓመት በዓልን በወሎ ግንባር ተገኝተው ከሰራዊቱ ጋር እያከበሩ ይገኛሉ።

በበዓል ማክበሪያ መድረኩ የተገኙት አቶ ብናልፍ አንዷለም እንዳሉት ፥ አሮጌው ዓመት በፈተና ውስጥ የታለፈ ቢሆንም በርካታ ድል የተመዘገበበት ነበር።

በአብነትም ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ እና የታላቁ የኢትዮጵያን ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በዓመቱ ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ይህ እንዳለ ሆኖ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ በሚል ቀቢጸ ተስፋ በተደጋጋሚ ጥቃት ፈጽሟል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሃት በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ በፈጸመው ክህደትና ጥቃት ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ እየደቆሱት እንደሚገኙ ገልጸዋል።

አሸባሪው ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ መፈጸሙን አስታውሰው፥ የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ሁሉ በመከላከያ ሰራዊት፣ በልዩ ሀይሎች ሚሊሻዎችና በህዝቡ እየተደቆሰ ህልሙ እንደ ጉም በኖ ጠፍቷል ብለዋል።

በዚህ ረገድ የወሎ ህዝብ ከሰራዊቱ ጋር ግንባር ድረስ ገብቶ አሸባሪውን ቡድን በመፋለም ታሪክ የማይረሳው ጀብድ መፈጸሙን ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ የድሬ ሮቃ፣ የፋጂ በአጠቃላይ የሀብሩ ነዋሪዎች ህያው ምስክሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

“አሸባሪው የህወሓት ቡድን ችግር ብቻ ሳይሆን መልካም እድልም ፈጥሮልናል” ያሉት አቶ ብናልፍ ፥ “ኢትዮጵያውያን በችግር ጊዜ የምንታወቅበትን እንደ አለት የጠነከረ አንድነታችን አሳይተንበታል”  ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

“በቀጣይ በ2014 ዓ.ም የሽብር ቡድኑን በአስተማማኝ ሁኔታ በመቅበር ኢትዮጵያን ወደ ልማትና ብልጽግና እናሻግራለን” ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.