Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለሕልውና ዘመቻው 25 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለሕልውና ዘመቻው 25 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን በከፈተው ወረራ የሕልውና ዘመቻ ላይ ለሚገኘው እና ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰበት የአማራ ክልል የደቡብ ክልል አጋርነቱን ገልጿል፡፡

በዚህም የደቡብ ክልል ሕዝብ የ25 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን አሚኮ ዘግቧል፡፡

ከተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ባለፈ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ምግብና ቁሳቁስ ተበርክቷል፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ርስቱ ይርዳው ዛሬ ጠዋት ባህር ዳር ገብተው ከክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር እና ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች ጋር መክረዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ርስቱ ይርዳው የሕልውና ዘመቻ የአማራ ክልል ዕዳ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊያን ሕልውና የመታደግ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው÷ ያደረግነው እና በቀጣይም የምናደርገው ድጋፍ ችሮታ ሳይሆን ግዴታ ነው ብለዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር የደቡብ ክልል ወንድም ሕዝብ ስላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች ንጹሐንን ጨፍጭፏል፤ የግለሰብ እና የመንግሥት ተቋማት ተዘርፈዋል፣ ወድመዋል፤ ነገር ግን አሸባሪውን ቡድን አስወግደን እና እናንተን የመሰለ ወንድም ሕዝብ ይዘን መልሰን እንገነባዋለን ነው ያሉት፡፡

አሸባሪ ቡድኑን ኢትዮጵያ እንደማትፈርስ መስዋዕትነት ከፍለን አሳይተነዋል ያሉ ሲሆን÷ ግባችን ይህን ኀይል ከአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ትከሻ ላይ ማውረድ ነው ብለዋል፡፡

ይህም በቅርቡ በድል ይጠናቀቃል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ደቡብ ክልል ሁሉም ሕዝብ በሰላም የሚኖርባት ትንሿ ኢትዮጵያ ናት ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ÷ ድጋፋችሁን የአማራ ሕዝብ ምንጊዜም አይረሳውም ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.