Fana: At a Speed of Life!

ታላቁ አሊምና ፈቂህ ሐጅ ሙሐመድ አልሳፊ አረፉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት ታላቁ አሊምና ፈቂህ ሐጅ ሙሐመድ አልሳፊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ ፡፡
ሸይኽ ሙሐመድ አልሳፊ ከሐጅ ሙሐመድ ሳኒ ሀቢብ ጋር ሆነው መጅሊስን ከመሰረታቸው በተጨማሪ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ሊቀመንበር በመሆን አገልግለዋል።
ሸይኽ መሐመድ አሳፊ አብዱረህማን የተወለዱት በቀድሞው አጠራር አርሲ ክፍለ ሃገር ሮቤ ከተማ አቅራቢያ ሲሆን÷ አባታቸው ከታላላቅ የአርሲ መሻይኾች አንዱ ሲሆኑ ስማቸውም ሼህ አብዱረህማን ሐጅ መሐመድ ሎጌ ይባሉ ነበር ።
ሸይኽ መሐመድ እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰም በዘመኑ ይሰጡ የነበሩ ሃይማኖታዊ እውቀቶችን ፊቅህ ፣ ነህው ፣ ሶርፍ ፣ በለጋ፣ መንጢቅ እና ተውሂድ ተምረዋል ።
ተፍሲረል ቁርዓን እና ሐዲስም በአርሲና በጅማ በሚገኙ ታላላቅ ዑለሞች ጋር መሔድ በርካታ ትምህርቶችን ቀስመዋል።
በውጭ ሃገርም ወደ ሳዑዲ አረቢያ በመጓዝ በአለም አቀፍ ደረጀ እውቅና ካላቸው የእስልምና ሃይማኖት ሊቃውንት ጋር ከእነ ሼህ አቡ ቱራቢ አልዘዋሂሪ እና ሼህ አብዱል ቃድር አስቀላኒ ጋር በመሆን በእስልምና ዙሪያ የቴሌቪዝን ፕሮግራሞችን ያቀርቡ ነበር።
1. ከሽፉ ስትሪል መስዱል ፊታሪሂ አል ‘ ሐበሸቲ ቢመሰሀ ሚነንቁል ( በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ )
2. አል አምበረቱል ሐበሽያህ ፊ ሲረቲ ነበውያህ ” ( በነብዩ መሐመድ ሰ.ዐ.ወ. ታሪክ ላይ የተመሰረተ ከ1000 ገፅ በላይ ያለው )
3. በመንፈሳዊ ህይወት ላይ የተመሰረተ (ቢሪቅየቱል መሲራት ፊ ኡሱሊ ሰዋቢል ቁርቢ ኢለል አምዋት)።
4. ፋኢደቱል ቢሪ ፊ ፈድሊ ዚክር ( ስለዝክር ትሩፋት የሚያነሳ)
5. የሃበሻና የአረቡን ዓለም የዘመናት ትስስር እና ታሪካዊ ግንኙነት የሚተነትኑ መጻሕፍትና በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን በመካከለኛው ምስራቅ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና ጋዜጦች ላይ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያን እና የሙስሊሞችን ታሪክ እያጣመሙ የሚፅፉ ግለሰቦችንም በየጊዜው በማስረጃ በመሞገት ይታወቁ ነበር።
ሸይኽ መሐመድ አልሳፊ ከልጅነታቸው ጀምሮ የሙስሊሙ ጉዳይ ያሳስባቸው ነበር ።
ከ40 አመት በፊት መጅሊስ እንዲቋቋም ጥረት ካደረጉ ሰዎች አንዱ ናቸው ።
ወጣቱ ከሃይማኖቱ ርቆ ፣ ባህሉን ረስቶ በስልጣኔ ስም ስነምግባሩ ተበላሽቶ እንዳይቀር ያሳስባቸዋል።
እስልምናውን አውቆ ለሃገሩ ጥሩ ዜጋ እንዲሆን ይፈልጋሉ ።
ዛሬ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ዓሊም በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ የማይናቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ።
በመጅሊስና በሌሎች እስላማዊ ተቋማት እንቅስቃሴ ምስረታ ትልቅ ድርሻ አላቸው ። ለእስልምና ባላቸው ተቆርቋሪነት ሳቢያ በርካታ ጊዜ ለእስርና ለእንግልት ፤ እንዲሁም ለስደት ተዳርገዋል ።
በዛም የተነሳ ለረጅም ጊዜ ታመው በህክምና ሲረዱ ቆይተው ዛሬ አርፈዋል ።
ሸይኽ መሐመድ አሳፊ ባለትዳር እና የልጆች አባት ነበሩ ።
የሼህ ሙሐመድ አልሳፊ የቀብር ስነ ስርአት ታላላቅ መሻኢኾች በተገኙበት ዛሬ ኮልፌ በሚገኘው መቃብር እንደተፈጸመ ከሸይኽኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.