Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ102 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የተመራ የብሔራዊ አስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባላትን ያቀፈ ልዑካን ቡድን በአፋር ለተፈናቀሉ ወገኖች በጥሬ ገንዘብና በአይነት ከ102 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ፡፡

ልኡካን ቡድኑ ዛሬ ሰመራ ከተማ በመገኘት ድጋፉን ለአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ አስረክቧል፡፡

ድጋፉ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና ቀሪው በአይነት የተደረገ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ድጋፉን ካደረጉት ተቋማት መካከል የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንና ትምህርት ሚኒስቴር ይገኙበታል፡፡

አቶ አወል አርባ “አሸባሪው ህወሓት በከፈተብን የእብሪት ወረራ ከፍተኛ መሠረተ-ልማትና ተያያዥ ተሰብአዊ ጉዳት አድርሷል” ብለዋል፡፡

“ቡድኑ በከፈተብንን ወረራ ያደረሰው ጉዳት እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጠላታችንን አውቀን በአንድነት ለሉአላዊነትና ለክብራችን እንድንቆም መልካም አጋጣሚዎ ፈጥሯል” ብለዋል፡፡

ክልሎችን ጨምሮ የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ለክልሉ ህዝብ ያሳዩት አጋርነትና ያደረጉት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ሚኒስቴሩ በአፋር ክልል ለተጎዱ ትምህርት ተቋማት ጥገና ማካሄጃ እንዲሆን 40 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው የብሔራዊ አስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል የሚኒስትሮች ኮሚቴ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመታደግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.