Fana: At a Speed of Life!

“ዘማች ወጣት” በሚል ርዕስ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ”ዘማች ወጣት”በሚል ርዕስ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ከመዲናዋ ከሁሉም ክፍለ ከተማዎች የተውጣጡ ወጣቶች እና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ታዳሚዎች በተገኙበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
 
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ አባል ሙሀዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ ከባድ ፈተናዎችን አልፋለች፤ አስቸጋሪ የሚባለው የቀይሽብር እና የነጭ ሽብር ታሪክ እንኳን አልፎ ዛሬ ላይ ደርሰናል፤ የአሁኑ ፈተናም ያልፋል ታሪኩ ይጻፋል።
 
በዚህ የሚያልፍ እና የሚጻፍ ታሪክ ውስጥ የእኛ ድርሻ ምን ይሁን የሚለውን ለይቶ ማወቅ ይገባል ያሉት ዲ/ን ዳንኤል፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተሳተፈበት ጦርነት ስለሆነና በድልም ስለሚቋጭ እንኳንም ይሄ ችግር ተፈጠረ የሚያስብል አዲስ ጠንካራ እና አንድ የሆነች ኢትዮጵያ ትፈጠራለች ብለዋል።
 
አገር ያለመስዋዕትነት እዚህ አልደረሰችምና እንደሰንደቋ ሁሉ ቀይም ቢጫም አረንጓዴም መስዋዕትነት መክፈል ይገባል ያሉት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፤ ቀዩ በግንባር የሚከፈለው መተኪያ የሌለው የህይወት ዋጋ፣ አረንጓዴው በኢኮኖሚው መስክ የሚከፈለው የደጀኑ ህዝብ ዋጋ ቢጫው ደግሞ በግንባርም በኢኮኖሚውም የሚከፈለው የአገር ዋጋ ነውና ሁሉም የሰንደቁን ዋጋ ልብ ሊለው ይገባል ብለዋል።
 
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት አገር ጦርነት ላይ ናት። ጦርነቱ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በሚፈልጉ ከሀዲዎች እና ኢትዮጵያን ለማዳን በሚፈልጉ የቁርጥ ቀን ልጆች መካከል ነው።
 
ጦርነቱ ፍትሃዊ ስለሆነ እንደምናሸንፍ ምንም ጥርጥር የለውም ያሉት አቶ ጌትነት፤ ይህ ጦርነት በአራት ግንባር የሚካሄድ ነው፤ አንደኛው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ሀይሎች እና ሚሊሻዎች የተሰለፉበት ግንባር ነው፤ ሁለተኛው የኢኮኖሚው ግንባር ሲሆን በአንድ እጅ ማረሻ በአንድ እጅ መሣሪያ ይዘው ለአገር የሚታገሉ ባለጠጎች የተሰለፉበት ነው፤
 
ሶስተኛው ግንባር የዲፕሎማሲው ሲሆን አራተኛው ደግሞ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ነው ያሉት አቶ ጌትነት፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከአራቱ በአንዱ የዘመተበት ጦርነት ስለሆነ የመጨረሻው ድል የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያዊያን ይሆናልና ሁሉም ሃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣ ብለዋል።
 
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ገና ከምስረታው ጀምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም አለመተማመንን በመፍጠር በምስራቅ አፍሪካ ላይ ጠንካራ አንድ የሆነች ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳትኖር ሲሰራ ኖሯል።
 
ይህንን እኩይ አላማውን ለማሳካት የከፈተው ጦርነት ኢትዮጵያዊያንን በታሪክ አጋጣሚ አንድ አድርጓቸዋል ያሉት ዶ/ር ቢቂላ፤ ጁንታው ያልፈጸመው ወንጀል ያልዘረፈው አካባቢ ባይኖርም ኢትዮጵያዊያን የትም መቼም በምንም እዘምታለሁ በሚለው አገራዊ ጥሪ ባሉበት ዘምተው አገርን እየታደጉ ናቸው ብለዋል።
 
የመከላከያ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በበኩላቸው፤ ወጣቶች ስሜት፣ እውቀት እና ጉልበት ያላቸው በመሆኑ መከላከያ በሥራው ሁሉ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ለወጣቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
 
ወጣቶች በወጣትነት ዘመናቸው ለአገራቸው አኩሪ ታሪክ መፈጸም አለባቸው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት፤ በታሪካችን የጀግንነትም የባንዳነትም ያለ ቢሆንም ወጣቶች የጀግንነት ታሪክን በመምረጥ ባሉበት ለአገራቸው ባንዳ የሆኑትን ከሀዲዎች መዋጋት አለባቸው ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.