Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል እየተወሰደ ባለው እርምጃ የዋጋ መረጋጋትና መቀነስ አሳይቷል-ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ እየተወሰደ ባለው እርምጃ የዋጋ መረጋጋትና መቀነስ መታየቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የከተማ ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
አንዳንድ ምርቶች ላይ ከ200 እስከ 1 ሺህ 500 ብር ቅናሽ መታየቱም ነው የተገለጸው።
የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ በክልሉ ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር ተወያይቷል።
በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ በክልል በአራት ዞኖች የሚገኙ የተለያዩ ከተማ አስተዳደሮችን መቃኘቱን የኮሚቴው የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ተናግረዋል።
በቅኝቱ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት አበረታች ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከክልሉ እስከ ወረዳ ድረስ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተቀናጀ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ መገንዘብ መቻሉን ተናግረዋል።
በከተሞቹ መጋዘኖች እየተፈተሹ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ሥራዎችና የንግድ አሻጥሮችን የመለየት ሥራ መከናወኑንም ጠቁመዋል።
ህገወጦች ላይ እርምጃ ከመውሰድ አንጻርም ከ50 ሺህ ብር እስከ ሦስት ወር በሚደርስ እሥራት የተቀጡ ነጋዴዎች መኖራቸውን የኮሚቴው ሪፖርት አመልክቷል።
የሕብረት ሥራ ማሕበራት ምርታቸውን በቀጥታ ለሕዝቡ በኤግዚቢሽን መልክ ማቅረብ መቻላቸው መልካም ጅምር መሆኑን አቶ ኡስማን ጠቅሰዋል።
በዚህ ሂደትም በተወሰኑ ከተሞች በአንዳንድ ሸቀጦች ላይ እስከ 1 ሺህ 500 ብር ድረስ የዋጋ ቅናሽ መታየቱን ተናግረዋል።
የሌሊት ድብቅ ንግድ መበራከት፣ የገበያ ትስስር ችግርና የምርት እጥረት ደግሞ አሁንም በንግዱ ስርዓት ላይ ማነቆ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዴንጌ ቦሩ በንግዱ ስርዓት ላይ እየታየ ያለው አሻጥር ፈተና መሆኑን በመገንዘብ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የኑሮ ውድነትን የሚከታተለው ኮሚቴ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
በተወሰደው እርምጃ ወደ 135 ሺህ የንግድ ተቋማት ተፈትሸው፤ ከ10 ሺህ በላይ በሚሆኑት ላይ የገንዘብና የእስራት ቅጣትን ጨምሮ የተለያዩ ህጋዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
እርምጃው ሥርዓት አልበኝነትን መግታት፣ የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋትና የዋጋ መቀነስ እንዲመጣ ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የከተማ ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ናቸው።
ህገወጥ የዋጋ ጭማሪ የኢኮኖሚ አሻጥር መሆኑን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በመሆኑም ህዝቡ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ህገ-ወጦችን በማጋለጥና ጥቆማ በመስጠት ሚናውን እየተወጣ ነው ብለዋል።
በክልሉ በተቋቋመው ኮሚቴ አማካኝነት በተከናወነ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ የዋጋ ማረጋጋት ብቻ ሳይሆን የተወሰኑ ምርቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ እንዲታይ ማድረጉንም ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.