Fana: At a Speed of Life!

የእስራኤል እና የኢትዮጵያን ዘመን መለወጫ ምክንያት በማድረግ ለህልውና ዘመቻው የድጋፍ  መርሃ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤል እና የኢትዮጵያን ዘመን መለወጫ ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያን ሕልውና ሰላምና አንድነት ለማስከበር  የድጋፍ ማስተባበሪያ መርሃ ግብር በእስራኤል ቴል አቪብ ተካሄዷል፡፡

በእስራኤል የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊያን፣ የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ለማስከበርና  ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ ለማሰባሰብ መርሃ ግብር ማዘጋጀታቸው ተገልጿል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ ዓለሙ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የከተማ ተወካዮች፣ ከተለያዩ ከተሞች የመጡ የድጋፍ አሰባሳቢ ቡድን አባላት ተገኝተዋል።

የአስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ  አቶ ሽሎሞ ሞላ የድጋፍ ማሰባሰብና የማስተባበር መርሃ-ግብር ሥራውን  በሚመለከት ባደረጉት ንግግር፥ የኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶች አገሪቱን ለማፍረስ ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል።

በዚህ ጊዜእኛ የቤተ እስራኤል ማኅበረሰብ አባላት እጃችን አጣጥፈን አንቀመጥም፣ የኢትዮጵያን ጉዳይ በቸልታ የምንተወው አይደለም፣ የተወለድንባት ያደግንባት አገራችን ሕልውና ፈተና ውስጥ ሲገባ ዝም አንልም ብለዋል።

በመሆኑም  በዚህ ወቅት ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ልንደርስላቸው ይገባልም ነው ያሉት።

ይህ የድጋፍ ማስባስቢያ መርሃ ግብር በየከተሞቹ እንደሚቀጥል ተገልጾ፥  ተሳታፊዎችም ከወገናቸው ጎን ለመቆም መነሳታቸውን አስረድተዋል።

አያይዘውም አያቶቻችን የተጋደሉላት የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት የሆነችውን የትውልድ አገራችን ሉዓላዊነት ለማስከበር ሙሉ ድጋፍ ለማድረግ ጠንክረን እንሰራለንም ሲሌ  አስታውቀዋል።

አምባሳደር ረታ ዓለሙ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፥ የሁለቱን አገሮች አዲስ ዓመት ያከበርነው በዚህ ሳምንት በመሆኑ እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ  ብለዋል።

ኢትዮጵያ እንደ እስራኤል የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት በመሆኗ፣ የራሷ ቋንቋ፣ የራሷ ፊደል፣ የዘመን አቆጣጠር ያላት መሆኑ የሁለቱ ሀገራት ትስስር ልዩ እንደሆነም ገልፀዋል።

አያይዘውም በአገራችን የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ጠንካራ መሰረት የተጣለበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶች  ሰላሟን  ለማደፍረስ አንድነታችን ለማናጋት የከፈቱብን ጦርነት ለመመከት የመከላከያ ሠራዊት፣ ሕዝብን ደጀን አድርጎ የአገርን ሕልውና ለማስከበር ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ትህነግ እና ሸኔ  አሸባሪዎች የጠላቶቻችንን አላማ ለማሳካት ኢትየጵያ እናፈርሳለን በማለት የጀመሩትን ጥቃት ለመቀልበስና የአገራችን ሕልውና ማስከበር በሚደረገው ትግል የዳያስፖራ አባላት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው መሆኑን አስረድተዋል።

መንግስት የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስከበር በሚያከናውናቸው ተግባራት በእስራኤል የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያን የጀመራችሁትን ሁለገብ ድጋፍ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ  ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኪነጥበብ ባለሙያዎች  በዕለቱን የሕዝቡን ወኔ የሚቀሰቅስና ወቅታዊ መልዕክት የያዙ ሙዚቃዎች  ማቅረባቸውን እስራኤል ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.