Fana: At a Speed of Life!

የሸድሆ መቄት ሆስፒታል በአሸባሪው ትህነግ ከ35 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የንብረት ዘረፋና ውድመት ደርሶበታል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሸድሆ መቄት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ከ35 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የንብረት ዘረፋና ውድመት እንደደረሰበት ተገለጸ።

አሚኮ እንደዘገበው የአማራ ባለሃብቶች አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን በሰሜን ወሎና በደቡብ ጎንደር ዞኖች ያደረሰውን የመሰረተ ልማት ውድመት ተመልክተዋል።

የፍላቂት ከተማ ነዋሪ አቶ አበራ ንጋቴ የደም ግፊት ሕመምተኛ ሲሆኑ÷ አሸባሪው ቡድን ባደረሰው ጉዳት በከተማው መድኃኒት በማጣታቸው ከሞት አፋፍ ላይ ደርሰው እንደነበር ተናግረዋል።

አካባቢው ከወራሪው ቡድን ነጻ ሲሆን መድኃኒት አግኝተው ህይወታቸው እንደቀጠለ ገልጸዋል።

ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለውን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ ሴት ወንድ ሳይባል ርብርብ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

ህዝብና መንግሥት ርብርብ በማድረግ በከተማዋ የሚገኘው ሆስፒታል ወደነበረበት ደረጃ እንዲመለስም ጠይቀዋል።

ሌላው አቶ ፀጋው ወረታ የጸረ ኤች አይ ቪ ኤድስ መድኃኒት ተጠቃሚና የነርቭ ሕመምተኛ ቢሆኑም በከተማቸው የሚገኘው ሆስፒታል በመውደሙና በመዘረፉ አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም።

በወረዳው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የጤና አገልግሎት ባለማግኘታቸው እየተጎዱ መሆኑን ገልጸው÷ መድኃኒት በማጣታቸው የጤና እክል እንደገጠማቸውም ተናግረዋል።

የሸድሆ መቄት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ይበልጣል ጌታ እንደተናገሩት÷ ሆስፒታሉ ከ35 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ዘረፋና ውድመት ደርሶበታል።

የሆስፒታሉ የራጅ ማሽን፣ ጠቅላላ የቤተ ሙከራ ማሽኖች፣ የቀዶ ሕክምና መሳሪያዎች፣ የአልትራሳውንድ ማሽኖች፣ የድንገተኛ ሕክምና ክፍል መገልገያ ማሽኖች፣ የማዋለጃ መሳሪያዎች፣ ሙሉ የሆስፒታሉ መድኃኒቶች እና ሌሎች በርካታ ቁሳቁስ ተዘርፈዋል።

በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ማቆሙን ሥራ አስኪያጁ ገልጸው÷ኅብረተሰቡና መንግሥት በጋራ ርብርብ በማድረግ ሆስፒታሉን ወደነበረበት እንዲመልሱም ጠይቀዋል።

የአማራ ባለሀብቶች በሆስፒታሉ የደረሰውን ዘረፋና ውድመት የተመለከቱ ሲሆን÷ በምልከታው ላይ የተገኙት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል÷ ጠላት ሆስፒታሉን ጨምሮ የተለያዩ ውድመቶችን መፈጸሙ የጭካኔውን ጥግ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

”ጠላትን ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል፤ አሸባሪ ቡድኑ እኛን ለማጥፋት ቆርጦ እንደተነሳው ሁሉ እኛም መቁረጥና መጨከን አለብን” ብለዋል።

አቶ መላኩ የአማራ ባለሀብቶች የተጎዳውን ኅብረተሰብ ለማጽናናትና ለመደገፍ ገረገራ ከተማ ድረስ መገኘታቸውን ገልጸው÷ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጎናቸው እንደቆመ አብራርተዋል።

ባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ “በየሰፈራችሁ መጥቶ ሊያጠፋችሁ የመጣውን ጠላት በመደራጀት ቀድማችሁ ልታጠፉት ይገባል” ብለዋል።

ወራሪው ቡድን የአማራ ክልልን ከወረረበት ጊዜ ጀምሮ ባለሀብቶቹ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አንስውም÷ የሚደረገውን ትግል በአሸናፊነት ለመወጣት እስከመጨረሻው ድጋፋቸው እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

“በቅርቡ በዚህ አካባቢ ለተጎዳችሁ የኅብረተሰብ ክፍሎች 800 ኩንታል ዱቄት እና የምግብ ዘይት ይደርሳችኋል፤ የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባትም የራሳችንን አሻራ እናስቀምጣለን፤ እናንተ ወገኖቻችን ሰላም ሳታገኙ በሰላም አንተኛም“ ነው ያሉት።

አቶ በላይነህ “ወራሪው ቡድን ገዳይ፣ ዘራፊና አውዳሚ በመሆኑ ብቻውን ነው የቆመው፤ እናንተ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችሁ ስለሆነ የአሸናፊነት ስሜት ሊኖራችሁ ይገባል ”ብለዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቀለመወርቅ ምሕረቴ ጠላትን ለመደምሰስ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ እንከፍላለን ብለዋል።

‘’ጠላት ወረራ ሲፈጽም አማራን ለመጉዳት እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ነበር፤ እኛም አሸባሪውን ቡድን ለማጥፋት ገደብ ሊኖረን አይገባም’’ ነው ያሉት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.