Fana: At a Speed of Life!

በመጠለያዎች የሚገኙ ዜጎችን ከመደገፍ ጎን ለጎን ቤት ለቤት ችግር ላይ የወደቁ ዜጎችን ለመድረስ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራና አፋር ክልሎች ልዩ ትኩረት የሚሹ ቦታዎች ያሉ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ግምገማ ተደርጓል፡፡
በዚህም በባህር ዳር እና ሰመራ ከተሞች የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከላት ተከፍተው ከ10 ክላስተሮች የተውጣጡ ተጨማሪ የባለሙያ ቡድኖች ወደቦታው መላካቸወ ተገልጿል፡፡
ከፊል ሰሜን ወሎ እና ዋግ ኸምራ ላይ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ዕለታዊ የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭት ተጀምሯል ነው የተባው፡፡
በመጠለያዎች የሚገኙ ዜጎችን ከመደገፍ ጎን ለጎን ቤት ለቤት ችግር ላይ የወደቁ ዜጎችን ለመድረስ የተጀመረው ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።
ቀደም ሲል ከተሰማራው 20 ተንቀሳቃሽ የሐኪሞች ቡድን በተጨማሪ ሌላ የህክምና ቡድኖች ለማሰማራት ከተለያዩ ክልሎች ጋር በመተባበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በአንዳንድ የአፋር፣ ሰሜን ወሎ እና ደቡባዊ ትግራይ አካባቢዎች የበረሃ አንበጣ ክስተት እየታየ በመሆኑ ሳይባባስ ለመከላከል ተጨማሪ የግብርና ባለሙያዎች እና ግብዓት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ወደስፍራው ለማድረስ ዝግጅት መጠናቀቁ ነው የተገለጸው፡፡
በተለያዩ ዘርፎች የተሰራው የመጀመሪያ ደረጃ የጉዳት ዳሰሳ ጥናት እንዳመላከተው÷ ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን ጨምሮ በርካታ የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች ተጎድተዋል፡፡
ከዕለት ደራሽ እርዳታ ጎንለጎን የመሰረተ ልማት መልሶ ግንባታና ማቋቋም ተግባራት ለማስጀመር ዝርዝር ጥናት የሚያደርግ ከመንግስት ተቋማትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጣ የሙያተኞች ቡድን ስራውን የሚጀምርበት የስራ መመሪያ መሰጠቱን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.