Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ብረት እና የተለያዩ ንብረቶቸ ተያዙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ባካሄደው ኦፕሬሽን በህገወጥ መንገድ የተከማቹ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የተለያዩ ንብረቶች መያዙን የፌዴራል ፖሊስ ገለፀ፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት በመዲናዋ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ፊናንስ ካምፕ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባካሄደው ኦፕሬሽን በአንድ መጋዘን ውስጥ ተከማችቶ የነበረና ከፍተኛ የዋጋ ግምት ያለው ንብረት መያዙን ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የተያዙት ንረቶችም ብረት፣ የከባድ መኪና ጎማዎችና የተለያዩ መጠን ያላቸው የፕላስቲክ ቱቦዎች መሆናቸውን ፖሊስ ገልጿል፡፡
ንብረቶቹን በምርመራ እያጣራ መሆኑን የገለፀው ፖሊስ÷ በዚህ ህገ ወጥ ድርጊት የተጠረጠረው ድርጅትም ዩናይትድ አልፋ ኮሜርሻል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሆኑን ደርሸበታለሁ ብሏል፡፡
አሸባሪው የህዋሃት ቡድን በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስና ሀገርን የማፍረስ እኩይ ተልዕኮውን ለማሳካት የተለያየ የኢኮኖሚ አሻጥር ሲሰራ መቆየቱና የወንጀል መረቦችንም ዘርግቶ በሀገር ደረጃ የሸቀጦች እጥረት እንዲፈጠር ማድረጉንም ነው ፖሊስ ያስታወቀው፡፡
በዚህ ሁኔታ በህገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ በህብረተሰቡ ጥቆማና በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር የዋሉት ንብረቶች በአብዛኛው ባለሃብቶቹ ከህውሓት ጋር ተሰልፈው ሀገር በማፍረስ ተልዕኮ ላይ የተሰማሩ ናቸው ተብሏል፡፡
ከተማ ውስጥ ባሉ ወኪሎቻቸው እያስነገዱ ገንዘብ የሚላክላቸውና ብሩንም ለከፈቱት ጦርነት አስፈላጊ ግብአቶችን ለማሟላት የሚጠቀሙበት ስለሆነ÷ ግለሰቦች የራሳቸውን ጥቅም ከሀገር በማስቀደም የግለሰቦችና የድርጅቶችን ማንነት ሳይለዩ ውክልና እንዳይቀበሉም አሳስቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.