Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ወደ ቻይና በሚደረጉ ጉዞዎች ላይ እገዳ መጣል ተገቢ አለመሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ወደ ቻይና በሚደረጉ ጉዞዎች ላይ እገዳ መጣል ተገቢ አለመሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገለፁ።

በቻይና የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመግታት ሀገራት ወደ ሀገሪቱ የሚደረጉ ጉዞዎችን እያገዱ፣ የንግድ ግንኙነቶችን እያቋረጡ እና አየር መንገዶችም ጉዞ እየሰረዙ መሆኑ ይታወቃል።

ዋና ዳይሬክተሩ ግን፥ ሀገራት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እንዲህ አይነት ውሳኔ ማሳለፋቸው ተገቢ አይደለም ሲሉ ተችተዋል።

ሁሉም ሀገራት በመረጃ ላይ የተመሰረተ እና ተገቢ የሆነ ውሳኔ እንዲያሳልፉም ጥሪ አቅርበዋል።

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ድንበር መዝጋት ስርጭቱን ከመቆጣጠር ይልቅ ሊያባብሰው ይችላል ብለዋል በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ ከገቡ ቫይረሱ ሳይታይ ሊሰራጭ እንደሚችል በማንሳት።

የቻይና ባለስልጣናትም የዓለም ጤና ድርጅት ምክረ ሀሳብን በመውሰድ ሌሎች ሀገራት እያሳለፉ ያለውን ውሳኔ ተቃውመዋል።

በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽህፈት ቤት የቻይና አምባሳደር ሊ ሶንግም፥ ሀገራት እየወሰዱት ያለው እርምጃ የዓለም ጤና ድርጅት ካወጣው ምክረ ሀሳብ ጋር የተቃረነ ነው ሲሉም ወቅሰዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ከታሕሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቻይና ውሃን ከተማ እንደተከሰተ ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን፥ ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ ቫይረሱ የዓለም ጤና ስጋት ነው ሲል ማወጁ ይታወሳል።

እስከ ዛሬ ጠዋት ባለው መረጃም በቻይና በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 425 የደረሰ ሲሆን፥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ከ20 ሺህ በላይ መድረሱ ነው የተገለፀው።

ቫይረሱ ከቻይና ውጪ የታየባቸው ሀገራት ቁጥርም 24 የደረሰ ሲሆን፥ በሀገራቱም ከ150 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን እና ከቻይና ውጪ በኮሮና ቫይረስ የተከሰተው ሞት 2 መድረሱንም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ምንጭ፦ reuters.com

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.