Fana: At a Speed of Life!

ለኢትዮጵያ ባንኮች ግማሽ ቢሊየን ዶላር ብድር ሊቀርብ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ (አፍሪ ኤግዚም ባንክ) ለኢትዮጵያ ባንኮች ግማሽ ቢሊየን ዶላር ብድር ለማቅረብ መወሰኑን አስታወቀ፡፡

የአፍሪ ኤግዚም ባንክ የደንበኞች ግንኙነት ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር ረኔ አዋምበንግ እንዳሉት÷ ባንኩ ከሌሎች አፍሪካዊ ባንኮች ጋር መወዳደር ሳይሆን በፋይናንስ ዘርፍ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ ለመፍታት ይሰራል።

እስካሁንም ከ25 ቢሊየን ዶላር በላይ በአፍሪካ ንግድ ፋይናንስ ዘርፍ ለፕሮጀክቶች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

ላለፉት ዓመታት በአፍሪካ መንግስታት ፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ ድጋፍ ሲያደረግ መቆየቱን ገልፀው÷ በኮቪድ-19 ወረርሽኝም ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ማቅረቡን ተናግረዋል።

አሁንም ተጨማሪ ለጸረ ኮቪድ 19 ክትባት ግዥ የሚውል ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማቅረብ ከአፍሪካ ህብረትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ባንኮች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ውድቀት ውስጥ ሆነው በፈጣን ለውጥ ላይ እንደሚገኙም ነው የጠቆሙት፡፡

ከ110 ሚሊየን ህዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያ በተለይም የአፍሪካ ቀንድ ምቹ ገበያ እንደሆነች ገለጸው÷ ባንኩ በፓን አፍሪካ ማዕቀፍ የአፍሪካ አገራት መካከል የሚደረግ የንግድ ልውውጥ እንዲሰጥ ድጋፍ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

ባንኩ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለተመታው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ማገገሚያም ሶስት ቢሊየን ዶላር ለባንኮች ድጋፍ መስጠቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተዘጋጀው መድረክ ዓላማም ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከር ስለመሆኑ አንስተዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት አጀንዳዎች ማስፈጸም በሚያስችሉ ዘርፎች ለመደገፍ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ባንኮች 500 ሚሊየን ዶላር ብድር ለመስጠት ባንኩ ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል።

ባንኩ ካሁን በፊት በኢትዮጵያ በተለያየ ዘር ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

በመስከረም መጨረሻም ሁሉም ሂደቶች ከባንኮች ጋር ከተፈጸሙ በኋላ ብድሩ እንደሚቀርብ ገልፀው÷ ለእያንዳንዱ ባንክ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚቀርብላችውም አሳውቀናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.