Fana: At a Speed of Life!

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ያሳችውን ቁርጠኝነት እናደንቃለን- ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፌ ሉቱንዱላ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ውይይታቸውም በአፍሪካ ህብረት አስተባበሪነት የሚካሄደውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ማስቀጠል በሚቻልበት ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ነበር ተብሏል፡፡
በወቅቱም አቶ ደመቀ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ሂደት ላይ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግስት ለተጫወተው የመሪነት ሚና አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝት ገልጸው÷ ይህም በሁሉም አካላት ዘንድ ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ላይ መድረስ እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ በኩል በማንኛውም ጊዜ በድርድሩ ለመሳተፍ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠውላቸዋል፡፡
ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲሰፍን በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ጽኑ ፍላጎት ገልጸው÷ ናይል የተፋሰሱ አገራት የትብብር እንጂ የግጭት መንስዔ መሆን እንደማይገባውም ተናግረዋል፡፡
ክርስቶፌ ሉቱንዱላ በበኩላቸው÷ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ላሳየችው ቁርጠኝት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መርህን አጥብቃ የምታምን መሆኗን ጠቅሰው÷ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድርም በዚሁ መርህ መመራት እንዳለበት እናምናለን ብለዋል፡፡
የሶስትዮሸ ድርድሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስጀመር የሚቻል ስለመሆኑም ገልፀዋል፡፡
አቶ ደመቀ በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ሂደት እስካሁንም ድረስ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከመግባባት ላይ በመድረስ ተጨባጭ ውጤት ያስመዘገበ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በቀጣይም ሂደቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማስቀጠል የሁሉንም ወገኖች ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገባ መፍትሔ ላይ መድረስ አንደሚቻል ኢትዮጵያ በፅኑዕ ታምናለች ማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.