Fana: At a Speed of Life!

በጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የወጣው መግለጫ የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፍ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የወጣው መግለጫ የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፍ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተገለጸ።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ጽህፈት ቤት አሉ በተባሉ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ የተጠናቀረው ሪፖርት በመጪው ጥቅምት ይፋ እንደሚደረግም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሳምንታዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን÷ በመግለጫቸውም በሳምንቱ የተከወኑ የተለያዩ ጉዳዮችን አስመልክተው አብራርተዋል።

ቱኒዚያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጉዳይ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ብትወስደውም ምክር ቤቱ ጉዳዩ የልማት ብቻ መሆኑን እንዳሰመረበትም ነው አምባሳደር ዲና የገለጹት።

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፌ ሉቱንዱላ ከኢትዮጵያ አቻቸው አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

የኮንጎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ ለዓባይ ፍትሃዊ አጠቃቀም ሆነ ለድርድሩ ያላትን ጽናት አድንቀው÷ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን የሚለውን መርህ ሃገራቸው አጥብቃ እንደምትደግፈው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አምባሳደር ዲና ቱኒዚያ የህዳሴው ግድቡን ጉዳይ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ብትወስደውም ምክር ቤቱ ጉዳዩ የልማት ብቻ መሆኑን አስምሮበታል ብለዋል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል የሃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የውሃ የመስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ጅቡቲን እና ኢትዮጵያን በሃይል ማስተሳሰር በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ ከጅቡቲ አቻቸው ጋር መወያየታቸውንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በጋራ ያካሄደው የሰብዓዊ መብት ጥናት የተጠናቀቀ ሲሆን÷ በመጪው ጥቅምት 22 ላይ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ልዑክ ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ጽህፈት ቤት ጋር ተወያይቷል።

ሆኖም ግን ሪፖርቱ ከመውጣቱ በፊት በአሸባሪው የህወሓትቡድን እና በሌሎች አካላት እየተናፈሱ ያሉ አሉባልታዎች ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቋል።

ኢትዮጵያ አሸባሪው የህውሓት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች እየፈጸማቸው ያላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአለም ዓቀፍ አካላት እና ሚዲያዎች ሽፋን እያገኙ አለመሆኑን ማሳወቋንም በመግለጫቸው ዳሰዋል።

የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የለውጥ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን እና በአሁኑ ወቅት ለዲፕሎማቶች፥ ቆንስላዎች እና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች እየተሰጠ ያለው የአስር ቀን ስልጠና የዚሁ አካል መሆኑን አምባሳደሩ አስረድተዋል።

በወንደሰን አረጋህኝ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.