Fana: At a Speed of Life!

የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ማእከል ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የባህል፣ ጥናትና ምርምር ማእከል ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራረመ።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብዙነሽ ሚደቅሳና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት ስምምነቱን ፈርመዋል።
የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የባህል፣ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ለይኩን በወቅቱ እንደገለጹት፤ ስምምነቱ የተፈረመው በአርት፣ በኪነ-ጥበብ፣ በቋንቋ ልማት እንዲሁም በአገር በቀል እውቀት ዘርፎች በትብብር ለመስራት ነው።
ስምምነቱ በእውቀት ዘርፎቹ በመማር ማስተማርና በጥናትና ምርምር በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።
ማዕከሉ በሚሰራቸው ስራዎች እስካሁን ከአራት ተቋማት ጋር የትብብር ስምምነት በመፈረም ድጋፍ እያገኘ መሆኑን ገልፀው፤ ለአብነትም የኮሪያው ኮይካ ድርጅት 32 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው፥ “ስምምነቱ በታላቁ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የባህል ማዕከል በኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ ታሪክ ላይ ሃሳብ እንድንለዋወጥና የስራ ግንኙነት እንድንፈጥር ያደርጋል” ብለዋል፡፡
“ጸጋዬ ገብረመድህን የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ዜጋ ሆኖ እንዲቀጥል በስነ ጽሁፍ አማካኝነት አስተሳሰብን በመቅረጽ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው” ብለዋል፡፡
በተለይ የስነ ጽሁፍ እድገት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ትልቅ መሰረት የጣሉ የስነ-ጽሁፍ ሊቅ መሆናቸውን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።
በስምምነት ፊርማ ስነ ስርአቱ ላይ ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.