Fana: At a Speed of Life!

ለአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ቡድን አባላት የእውቅና መርሐግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)ለ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ላለፈው የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ቡድን አባላት የሽልማት እና የእውቅና መርሐግብር ተካሄደ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ቡድን በሱፐር ሊግ አሸናፊ በመሆን ወደ የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ በመሸጋገሩ ከፍተኛ ኩራት እና ደስታ ተሰምቶኛል ያሉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ቡድኑ ያስመዘገበው ውጤት የጥረት፣ የአንድነት እና የታታሪነት ምልክት ነው ብለዋል፡፡

በከፍተኛ ጥረት፣ በጠንካራ የቡድን ስራ እና ትብብር ይህን ውጤት ላስመዝገባችሁ የእግር ኳስ ቡድኑ አባላት በራሴ እና በከተማችን ነዋሪዎች ምስጋና ይገባችኋል ያሉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ አመርቂ ውጤት እንድታስመዘግቡ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ሱፐር ሊግ ተወዳድረው በየምድባቸው አንደኛ ደረጃን በመያዝ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ላለፉት የቡድኑ አባላት ለእያንዳንዳቸው እስከ 200 ሺህ ብር በጠቅላላው የአምስት ሚሊየን ብር የማበረታቻ ሽልማት መሰጠቱን የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር በላይ ደጀን ገልጸዋል፡፡

ማምሻውን በተካሄደው የሽልማት እና እውቅና መርሐግብር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማዋ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ፣ ከፍተኛ አመራሮች እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች መገኘታቸውን ከከተማው ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.