Fana: At a Speed of Life!

በአሸባሪው ትህነግ ለተጎዱ ዜጎች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አፋጣኝ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ጋር በመተባበር በክልሉ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በከፈተው ወረራ የተፈናቀሉ እና አፋጣኝ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎችን ለመታደግ ያለመ ምክክር ተካሂዷል፡፡
በምክክር መድረኩ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች እና የስደተኞች ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተወካዮች ታድመዋል፡፡
በምክክር መድረኩ በክልሉ ከአምስት ዞኖች የተፈናቀሉ እና አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች ለከፋ የሰብዓዊ ችግር ተጋልጠዋል ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከአሸባሪው ቡድን በደረሰባቸው ወከባ አካባቢያቸውን ለቀው ወጥተው በተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው የሚገኙ የክልሉ ዜጎች የምግብ፣ ሕክምና፣ መጠለያ እና የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግሮች ገጥሟቸዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ካትሪን ሱዚ ድርጅታቸው የምግብ እና ምግብ ነክ ካልሆኑ ድጋፎች በተጨማሪ የቴክኒክ ድጋፍም ያደርጋል ብለዋል፡፡
የሰብዓዊ ድጋፉ አሳሳቢ እና በአስቸኳይ መድረስ ያለበት እንደሆነ ተረድተናል ያሉት ዶክተር ካትሪን በተቻለ ፍጥነት ከአጋሮቻቸው ጋር በትብብር ለማድረስ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡
ሰብዓዊነት ድንበር የለውም ያሉት ዶክተር ካትሪን በችግሩ ስፋት እና ውስብስብነት መጠን ለእናቶች፣ ሕጻናት፣ ሴቶች እና አረጋዊያን ለመድረስ እንሠራለን ብለዋል፡፡
በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት መረጃዎች በአግባቡ ተጣርተው እና ተሟልተው ሊቀርቡ ይገባልም ነው ያሉት፡፡
የአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን በፈጸመው ወረራ በክልሉ ያሉ ተፈናቃዮች ለከፋ የሰብዓዊ ጉዳት ተዳርገዋል ያሉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር በተለይም አሸባሪው ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡
የምግብ እና መድኃኒት አቅርቦት እንዲደርሳቸው ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለተፈናቃዮች፣ አሸባሪው ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች እና ነፃ በወጡ አካባቢዎች ለሚደረግ መልሶ ግንባታ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሰበሰበው ድጋፍ አበረታች ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር የፌዴራል ተቋማት እና መንግሥት ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸውም ነው ያሉት፡፡
ምክክሩ ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶችን በተናጠል ከማግኘት ባሻገር በተሰባሰበ መንገድ ማግኘቱ የተሻለ አማራጭ ሰጥቷል ያሉት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ናቸው፡፡
የሰብዓዊ ድጋፍ በቅርቡ የሚደርስበትን አማራጭ ጉዳዮች እንደቀረቡበትም አንስተዋል፡፡
መልሶ ግንባታው ላይ የፌዴራል መንግሥት እና ማኅበረሰቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ የሚያጠናክር አቅም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.