Fana: At a Speed of Life!

ባህሬን የኢትዮጵያን ምርቶች ለመግዛት ፍላጎት እንዳላት ገለፀች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህሬን የንግድንና ኢንዱስትሪ ቻምበር የኢትዮጵያን ምርቶች በብዛት ለመግዛት ፍቃደኛ መሆኑን ገለጸ፡፡

በባህሬን የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር ጀማል በከር ከባህሬን የኢንዱስትሪና የንግድ ቻምበር የምግብ ሀብት ኮሚቴ ሊቀ መንበር አቶ ካሊድ አሊ ራሽድ ጋር የሁለቱ አገራት የኢንቨስትመንት፣ የንግድ፣ የቢዝነስና የቱሪዝም ትብብርን በሚያጠናክሩበት ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

አምባሳደር ጀማል በከር በሀገራችን ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎች፤ ማበረታቻዎች፤ የአንድ መስኮት አገልግሎትና የታክስ እፎይታ እንዲሁም በሪፎርሙ ምክንያት የተደረጉ የህግና የአስራር ማሻሻያዎች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በተመሳሳይ የሀገሪቷን የማኑፋክቻሪንግ፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግና የግብርና ምርቶች በተለይም የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ፣ አበባ፣ ቡና፣ ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ ቅመማቅመም እና የባሕል አልባሳት በባህሬን ገበያ በሚቀርቡበት ጉዳይ ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

የባህሬን የኢንዱስትሪና የንግድ የምግብ ሀብት ኮሚቴ ኃላፊ የሆኑት አቶ ካሊድ አሊ ራሽድ በበኩላቸው የተደረገላቸውን ገለጻ አድንቀው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዘርፋ ብዙ የንግድ፤ የኢንዱስትሪ፤ የኢንቨስትመንት፤ የቱሪዝም ትስስርና ትብብር ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት ያላት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው÷ ሀገራቸው 90 በመቶ የሚሆነውን የምግብ ፍጆታ ከውጪ የምታስገባ መሆኑ ገልጸው የኢትዮጵያን የማኑፋክቻሪንግ፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግና የምግብ ምርቶች በባህሬን ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲገቡ አስፈላጊውን ትስስርና ትብብር ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎቶች በብዛትለመግዛትም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የተጀመረው ግንኙነትና ትብብር ይበልጥ እንዲጠናከር ከኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር የተለዋወጡትን የመግባቢያ ሰነድ በመፈረም የሁለቱ የወንድማማቾችና እህትማማቾች ሀገራት ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ዙሪያ በቅንጅትና በትብብር ለመስራት የጋራ መግባባት መፈጠሩን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.