Fana: At a Speed of Life!

ህብረተሰቡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከያዎችን በአግባቡ ሊተገብር ይገባል-የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ አስተዳደር የኮቪድ -19 ወረርሽኝ እንደ አዲስ በመቀስቀሱ ህብረተሰቡና የትምህርት ተቋማት የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ እንዲተገብሩ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ አሳሰበ።

በተያዘው ሳምንት ብቻ በኮሮና ቫይረስ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተመልክቷል፡፡

የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ ባለፉት ሁለት ወራት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ የነበረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በአሳሳቢ ሁኔታ ጨምሯል፡፡

በድሬዳዋ በተለያዩ የግልና የመንግስት ሆስፒታሎች በአምስት ቀናት ምርመራ ከተደረገላቸው 987 ሰዎች መካከል 179ኙ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሣምንት ብቻ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የ5 ሰዎች ህይወት ማለፉንም ተናግረዋል።
በነሐሴ ወር የወረርሽኙ የስርጭት መጠን 3 ነጥብ 1 በመቶ እንደነበረም ኃላፊዋ አስታውሰዋል፡፡

ወይዘሮ ለምለም አክለው እንደተናገሩት አሁን በድሬዳዋ እየተስፋፋ ያለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገዳይ የሆነውና ዴልታ የተባለው የቫይረስ ዝርያ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ ያለምንም መዘናጋት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛን በመልበስና የመከላከያ በአግባቡ መንገዶችን በመተግበር ራሱን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።

ተማሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ፣ እጅን በውሃና ሣሙና አዘውትሮ መታጠብንና ተራርቀው በመቀመጥ ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሀመድ በበኩላቸው “አምና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በትምህርት ቤቶች ሲደረጉ የነበሩ ጥንቃቄዎች ዘንድሮም ይተገበራሉ” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.