Fana: At a Speed of Life!

በሀገሪቱ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የሚጠጋ ተጨማሪ ስንዴ ይመረታል -ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የሚጠጋ ተጨማሪ ስንዴ ለማምረት እንደሚሰራ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የ2013 የግብርና ሥራ አፈፃፀምና የተያዘው የስራ ዘመን አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ አካሂዷል ፡፡

በዚህ ወቅት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን እንደተናገሩት፤ ከውጪ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ አምርቶ ለመተካት በተለይ ከአምና ጀምሮ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።

ስራው ከክልል ክልል የአፈፃፀም ልዩነት ቢኖረውም አበረታች ውጤት የተገኘበት ነው ያሉ ሲሆን ÷በበጋ መስኖ ብቻ በ400 ሺህ ሄክታር ፤ በበልግና ክረምት ደግሞ 300 ሺህ ሄክታር ላይ ስንዴ እንደሚመረት ገልጸዋል፡፡

በዚህም እስከ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ተጨማሪ ስንዴ በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት ሙሉ በሙሉ ለመተካት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ሥራዎች በቅንጅት ከተመሩ የስንዴ ምርትን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የመተካቱ ዕቅድ በአንድ ዓመት ውስጥ መሳካት የሚችል ነው ብለዋል።

አርሶ አደሩን ከገበያው ጋር የሚያስተሳስር የፋይናንስና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ አሰራሮች መዘርጋት እንዳለባቸው መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በበልግ ወቅት ባጋጠመው የዝናብ እጥረት፣ በጸጥታ ችግርና በሌሎች ምክንያቶች ምርት ያልተመረተባቸው ማሳዎች በመኖራቸው በዚህ ሳቢያ ሊከሰት የሚችልን የምርት እጥረት ለማካካስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.