Fana: At a Speed of Life!

 በየካቲት ወር መጀመሪያ  ለሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 26 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በየካቲት ወር መጀመሪያ ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ከየካቲት 1 እስከ 2 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄደውን የአፍሪካ ህብረት መሪዎች መደበኛ ጉባኤ አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑን በሚኒስቴሩ የፕሮቶኮል ጉዳዮች ተጠባባቂ ዳሬክተር ጄነራል አቶ ግስላ ሻወል ገለፀዋል፡፡

33ኛው የመሪዎች ጉባኤ “ግጭትና ጦርነትን በማስቆም ለአፍሪካ ልማት ምቹ ሁኔታን ማመቻቸት”በሚል መሪ ቃል ለሁለት ቀን እንደሚካሄድ ነው የተነገረው።

ከህብረቱ መደበኛ ጉባኤ በፊትም ከጥር 28-29 ቀን 2012 ዓ.ም የሚቆይ የሚኒስትሮች ስብሰባ ይደረጋል ነው ተባለው፡፡

በጉባኤው ላይ ለመሳተፍም ከህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች በተጨማሪ የሌሎች ሃገራት መሪዎች ይገኛሉ ተብሏል።

በዚህም ከአባል ሃገራቱ የ31 ሀገራት ፕሬዚዳንቶች፣ አራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ የሰባት ሃገራት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የሶስት ሃገራት ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ 14 ቀዳማይ እመቤቶችን ጨምሮ 45 ሃገራት በስብሰባው ላይ እንደሚሳተፉ ማረጋገጫ  መስጠታቸውን አቶ ግስላ ተናግረዋል፡፡

ከአባል ሀገራት ውጪ የካናዳ፣የኖሮዌ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ፣ የፍልስጤሙ ፕሬዚዳንት ፣የሶስት ሀገራት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የሰባት ሀገራትት አምባሳደሮች እንደሚሳተፉ በመግለጫው ተመላክቷል።

በአጠቃላይ እስካሁን 8 ሺህ 700 ተሳታፊዎች የተመዘገቡ ሲሆን እስከ በጉባኤው 10 ሺህ እንግዶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በጥበበስላሴ ጀበሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.