Fana: At a Speed of Life!

ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የአሜሪካ ኮንግረስ ልዑክን በጽ/ቤታቸው አነጋገሩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒሰትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ካረን ባስ የሚመራ ልዑክ በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሚኒስትሯ ቢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ከምንጩ ለመስማትና ለመረዳት በመምጣታቸው አመስግነው የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ውሳኔ ከማድረጉ በፊት እና በኋላ የሰብዓዊ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የተደረጉ ጥረቶችን በዝርዝር አስረድተዋል።
ሰብዓዊነት አድሎን አይፈልግም ያሉት ሚኒስትሯ፣ በህወሃት ወረራ ምክንያት ለተጎዱ በሁሉም ስፍራ ለሚገኙ ወገኖቻችን ሁሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማዳረስ እያደረግን ያለው ጥረት እንደመንግስት አጠናክረን እንቀጥላለን ሰብዓዊ አጋሮችም ይህንኑ እንዲያደርጉ እንጠብቃለን ብለዋል።
ሚኒስትሯ የአሜሪካን መንግስትን ጨምሮ አንዳንድ አጋር ሀገራት ከለውጥ ማግስት ያስመዘገብናቸውን ከፍተኛ ድሎች ለመመስከር አለመድፈራቸውን በተለይም ከተተነበየልን በተቃራኒው በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ኢትዮጵያ ማሸነፏን እውቅና መስጠት አለመድፈር እንቆቅልሽ ነው ብለዋል።
አክለውም አጋሮቻችን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ እንዳላየና እንዳልሰማ ለማለፍ ቢሞክሩም አሁንም የተቃጣብንን ወረራ ከመመከት ጎን ለጎን ዜጎቻችንን ከችግርና መፈናቀል ለመታደግ የምናደርገው ጥረት የሰውነት እና የመንግስትነት ግዴታችንን መወጣት በመሆኑ ለአፍታም የምንዘናጋበት ጉዳይ አይደለም ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።
ሰብዓዊ እርዳታን በፍጥነት ለማድረስ እንዲሟሉ በሰብዓዊ አጋሮች የተጠየቁ ቅድመ-ሁኔታዎችን ሁሉ ብናመቻችም እስከ አሁንም ቢሆን አለም አቀፍ ድርጅቶች በተገቢው መጠንና ፍጥነት ለተጎዱ ወገኖቻችን ለመድረስ በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት እየተንቀሳቀሱ አይደለም ይህም ያሳስበናል ብለዋል።
በተደጋጋሚ እንዳሳወቅነው በአማራ እና አፋር ክልሎች የእለት እርዳታ የሚሹ ወገኖቻችንን ቁጥር ከዕለት ዕለት እየጨመረ በመሆኑ በተለይም መንግስት መድረስ በማይችልባቸው አካባቢዎች የተመረጡ አጋሮች እርዳታን እንዲያደርሱ በተደረገው ስምምነት መሰረት አፋጠኝ ምላሽ እንዲሰጡ ስለመጠየቃቸው ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.