Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ያስተላለፉትን ትዕዛዝ ሊሰርዙ ይገባል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ያስተላለፉትን ትዕዛዝ ሊሰርዙት እንደሚገባ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት ጠየቀ።

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን ሁኔታ ያልተገነዘበ ነው ያለውን የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የማዕቀብ ትዕዛዝ አጥብቆ እንደሚያወግዘው አስታውቋል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው አሸባሪው የህወሃት ቡድን የሀገሪቱ የሰላምና ደህንነት እንቅፋት ሆኖ ሳለ፤ መንግስት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ በወሰደው እርምጃ ምክንያት ማዕቀብ መጣል ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት አባል እና ዓለም አቀፍ ሕግን በማክበር የውስጥ ጉዳይወን በራሷ የመፍታት ሙሉ መብት ያላት ሉዓላዊ ሀገር ነች ብሏል ምክር ቤቱ በመግለጫው።

የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር ባስተላለፈው ኢፍትሃዊ ውሳኔ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በግልጽ ጥሷል ያለው ምክር ቤቱ፥ ለዚህም ማሳያው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “አሸባሪ” ብሎ ከፈረጀው ቡድን ጋር መንግስት እንዲወያይ መጠየቁ ነው ብሏል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ድንገት በማጥቃት ከትግራይ ክልል በጎረቤት ክልሎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመፈታተን ላይ ይገኛል ነው ያለው ምክር ቤቱ።

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍን ለማጠናከር የተኩስ አቁም ቢያውጅም አሸባሪው ቡድን የተኩስ አቁም ውሳኔን እራሱን በማደራጀት ተጠቅሞበታል ያለው ምክር ቤቱ ፤በዚህም በአማራ እና አፋር ክልሎች በርካታ የሲቪል ዜጎች ግድያ ፈጽሟል እንዲሁም የመሠረተ ልማቶችን አውድሟል።

አሸባሪው ቡድን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በማይካድራ ጭና፤ጋሊኮማ፤አጋምሳ ከመጨፍጨፉ በተጨማሪ በወረራቸው ክልሎች ውስጥ የሰብዓዊ ቀውስ እንዲከሰት አድርጓል።

እንዲሁም ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናትን ፣ ሆስፒታሎችን እና ትምህርት ቤቶችን አውድሟል ሲል የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ዜጎች ምክር ቤት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የአሸባሪው ህወሃት ቡድንን አጥፊ አካሄድ ከመከላከል አልፎ ቡድኑ ለፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ለሰጠው ምላሽ ከባይደን አስተዳደር አድናቆት ይገባው ነበር ሲል ገልጿል።

የባይደን አስተዳደር የአሸባሪው ቡድንን ማውገዝ ሲገባው የማዕቀብ ትእዛዝን መስጠቱ ስህተት ነው ያለው ምክር ቤቱ የተላለፈውን የማዕቀብ ውሳኔ ሊሰርዝ ይገባል ሲል መጠየቁን ኢዜአ ዘግቧል።

በመሆኑም የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር ከአሸባሪ ቡድን ጋር ድርድር እንደማይኖር ተገንዝቦ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስት ጋር ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ቢያጠናክር የተሻለ ይሆናል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው የፕሬዝዳንቱ የማዕቀብ ውሳኔ የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ይጎዳዋል ያለ ሲሆን ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምም የሚያበረክተው አስተዋጽዎ አይኖርም ብሏል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.