Fana: At a Speed of Life!

በአሜሪካ የሚኖሩ የእስቴ ወረዳ ተወላጆች በሽብር ቡድኑ ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ አደረጉ

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የሚኖሩ የእስቴ ወረዳና የአካባቢዋ ተወላጆች በሽብር ቡድኑ ለተጎዱ ዜጎች ከ675 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቀለመወርቅ ምሕረቴ በውጪ ሀገር የሚገኙ የእስቴና የአካባቢው ተወላጆች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ተወላጆቹ በተወካያቸው አማካይነት በአካል በመገኘት ያደረጉት ድጋፍ በታሪክ ይመዘገባል ነው ያሉት። ለወደፊትም ለወገኖቻቸው የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።

ጠላት ያለ የሌለውን ኃይል አሰባስቦ በእስቴ አካባቢ ቢመጣም የአካባቢው ማኅበረሰብ ውርደትን እንዲከናነብ አድርጓል ብለዋል አቶ ቀለመወርቅ ። ጠላት በጉና ተራራ ላይ በታሪክ የማይረሳ ውርደትን ቀምሷል ነው ያሉት።

“ልጆቻችሁን በመመረቅ ወደ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በማስገባት የሀገራችሁን ሉዓላዊነት ማስከበር ይኖርባችኋል” ሲሉም አሳስበዋል።

አክለውም “የሀገር መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀል የራስን ክብር ማስጠበቅ ነው፣ ጠንካራ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ግንባታ እንዲኖር የምናደርገው እኛው ነን” ብለዋል።

በህልውናው ዘመቻ በርካታ በታሪክ የሚመዘገቡ ጀግኖች መፈጠራቸውንም ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።

ዞኑ በሚችለው አቅም ሁሉ ለህልውናው ዘማች ተጎጂዎች ድጋፍ እንደሚያደርግም ዋና አስተዳዳሪው ቃል ገብተዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ “ጠላት በእስቴ ወረዳ ጥሶ ለመግባት ቢሞክርም የአካባቢው ጀግኖች በመጣበት እንዲመለስ በማድረጋቸው ሊደነቁ ይገባል” ብለዋል።

አሁንም ጠላት ሙሉ በሙሉ ስላልተደመሰሰ በዞኑ የሚገኙ ሕዝቦች መደራጀት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የድጋፉ አሰባሳቢና ተወካይ አቶ ጌትነት ይስማው እነዚህን የሀገር አለኝታ የሆኑ ጀግኖችን መደገፍ ታላቅ ኩራት ነው ብለዋል።

የዞኑ መሪዎች ለህልውናው ዘመቻ ላደረጉት ተጋድሎ ሊመሰገኑ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

አቶ ጌትነት የሚያደርጉት ድጋፍም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.