Fana: At a Speed of Life!

የኦሞ ወንዝ ውሃ ሙላት ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ ውሃ ሙላት ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ።

የኦሞ ወንዝ ከወራት በፊት ከመፍሰሻው መስመር ወጥቶ በአካባቢው የሰፈሩትን ከማፈናቀል አልፎ በሰው ላይ እስከ ሞት ጉዳት፣ በንብረትና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማምጣቱ ይታወሳል፡፡

አሁን ደግሞ ከባለፈው ከፍ ያለ ይዘት ያለው ውሃ በአካባቢው ጉዳት እያመጣ ይገኛል፡፡

የዞኑ አመራሮች በውሃ ሙላት የተፈናቀሉትንና የተጎዱ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል፡፡

እንደወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀብራራው ተክሌ ገለጻ ከ62 ሺህ በላይ የተፈናቀሉ ዜጎች እንዳሉ ከእነዚህ መካከል 36 ሺህ 92 ዜጎች ደግሞ በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

አርብቶ አደሩ ከብቶቹን እንደዋነኛ ሃብት የሚጠቀም እንደመሆኑ መጠን የውሃው ሙላት ከግጦሽ ውጭ ስላደረጋቸው የተጋረጠባቸው ችግር በቀላሉ የሚገመት አይደለም ሲሉም አክለዋል፡፡

ከ6ሺህ በላይ እናቶችና ሕጻናት ተፈናቅለዋል፣ በ2 መቶ 8 ሄክታር መሬት ላይ ያለ ሰብል ለመውደም ችሏል፣ ሁለት የመስኖ አውታሮች፣ ሁለት ጤና ኬላዎች፣ ሁለት የእንስሳት ጤና ክሊኒኮች፣ አራት የውሃ ፓምፖችና በኮሮ ብቻ 3መቶ 67 ቤቶች ከፍተኛ ጉዳት እና ሌሎች ደርሶባቸዋል፡፡
ከምንም በላይ አርብቶ አደሩን ከውሃ ውስጥ ማውጣት ከማንኛውም ተግባር የሚቀድም በመሆኑ በወረዳው በጀት የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ እንደሚገኙ ዋና አስተዳዳሪው መግለጻቸውን ከደቡብ ኦሞ ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወረዳው በተደጋጋሚ በዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ችግሮች ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረገና ከልማት ሥራ እየተስተጓጎለ በመሆኑም ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ ብቸኛ አማራጭ ነው ብለዋል፡፡

በሥፍራው የተገኙት የክልሉና የዞኑ አደጋ ስጋት መካላከል ባለሙያዎች እንደተናገሩት÷ በወቅቱ ለማኅበረሰቡ መድረስ ያለበት መደበኛ የእርዳታ እህል ከሃምሌ ጀምሮ ባለመድረሱ ችግሩን የበለጠ ያባብሰዋል፡፡

ባለሙያዎቹ አክለው ይህ ችግር ትኩረት ያለመስጠትና ለወረዳው ብቻ የመተው ጉዳይ ያለውን ሁኔታ ያባብሰዋል እንጂ መፍትሔ ሊሆን ስለማይችል ከጤና እና ከሌሎች የሚመለከታቸው ቢሳተፉበት የተሻለ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የዞኑን ግብረ-ሃይል የመሩት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አረጋ እንደተናገሩት÷ ዞኑ በቅርበት ሆኖ እንደሚደግፋቸውና ወረዳው የያዘውን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያደርገውን ሃሳብ አድንቀዋል፡፡

ጉዳቱ በቀጣይ በሰውና እንስሳት ጤና ላይ ሊያስከትል የሚችለውን በመገምገም የሚመለከተው አካል ከወዲሁ የጥንቃቄ ሥራ እንዲሰራና መፍትሔውን በጥናት እንዲደገፍ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪ አቶ መሰለ መስፍን አሳስበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.