Fana: At a Speed of Life!

በሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ብስለት በተሞላበት አካሄድ እየተተገበሩ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ብስለት በተሞላበት አካሄድ ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ገለፁ፡፡

ዶክተር እዮብ ይህን ያሉት እየተተገበረ ባለው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ኢንቨስትመንት እና የኢትዮጵያ አመችነት ዙሪያ ላይ ያተኮረ ስልጠና ለውጭ ጉዳይ ለዋናው መስሪያቤት ሰራተኞች፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች ፣ ተጠሪ ተቋማት፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር እና ከተለያዩ ተጠሪ ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎች በተሰጠበት ወቅት ነው፡፡

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ኢንቨስትመንት እና የኢትዮጵያ አመቺ ሁኔታዎች ላይ ለሰልጣኞች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ማድረጊያ መንገዶችን ከተጨባጩ የዓለም ተሞክሮ አኳያ አቅርበዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ላይ ለግብርና፣ ለማምረቻው ዘርፍ፣ ለማዕድን፣ ለቱሪዝም እና ለአይ ሲቲ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከአሁን በፊት በመንግስት ቁጥጥር ስር ብቻ የነበሩ ዘርፎች ጥንቃቄ በተሞላበት አካሄድ ወደ ግሉ ዘርፍ እየተዘዋወሩ እና በሂደት ላይ መሆናቸውን አብራርተው እንደ ማሳያም የቴሌኮም ዘርፉን አንስተዋል፡፡

አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው÷ ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ ለውጭ ኢንቨስትመንት አመቺ የሆነችባቸውን ዘርፎች ለይተው ከኩባንያዎች ሊቀርቡ የሚችሉ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል ግንዛቤ እና ክህሎት መታጠቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ከሌሎች ሀገራት የቀሰሟቸውን ልምዶችንም ለሰልጣኞች አካፍለዋል፡፡

በሰልጣኞች የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን÷ በአቅራቢዎች እና ሥልጠናውን በመሩት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሾነር ሌሊሴ ነሜ ምላሽ መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.